FOR BETTER OROMIA

አቶ ልደቱ አያሌው – በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ ዙሪያ

“ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙኃን አስተሳሰብ ተጨፍልቋል”

ባለፉት 4 ወራት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ተቃውሞና ግጭት እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ
አካባቢዎች የተከሰቱ ብጥብጦችን አስመልክቶ አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፤ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሚከተለውን ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

e206d320f47bf57e095578796b3b640d_Mዘንድሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለምን ተቃውሞና ግጭቶች የበዙ ይመስልዎታል?
የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመርን አንስቶ፣ ስርአቱ እንደ ስርአት ያለው አቅጣጫ ልዩነት ላይ የሚያተኩር ስለሆነ፣ በሂደት የህዝብን ትስስርና አብሮ የመኖር ሁኔታ እየሸረሸረ፣ ግጭቶችን እንደሚያባብስ ስንገልፅ ነበር፡፡ በአንፃሩ ኢህአዴግ የያዝኩት መንገድ ይበልጥ የህዝቡን አንድነት የሚያጠናክር ነው የሚል አቋም ላለፉት 25 አመታት ይዞ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት የሰላም ኮንፈረንስ ሲያካሂድ ነው የኖረው፡፡ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ አልታየም፡፡ አሁን ደግሞ በመጠኑም ሆነ በይዘቱ አቅጣጫውን የቀየረ አስቸጋሪ ሁኔታ በሀገሪቱ እየተፈጠረ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ከአሁን በፊት ግጭት ብቅ ይላል፤ ብዙም ሳይታይ ይዳፈናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብቅ ይላል፡፡

አሁን ግን ቀጣይ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በብዙ አካባቢዎች እያየን ነው፡፡ ኢህአዴግ በአጠቃላይ በህዝቦች አንድነት ላይ ሳይሆን ለልዩነት ትኩረት ሰጥቶ የሚያራምደው ፕሮፓጋንዳ፣በሂደት ውጤቱ ምን እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በቀጥታ ከፌደራል ስርአት አደረጃጀቱ ጋር ይያያዛል፤ቋንቋና ብሄርን መሰረት አድርገው ከተደራጁ ፓርቲዎች አጠቃላይ ሁኔታም ጋር ይገናኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ችግሮቹ ለምን እየተባባሱ መጡ?
አንዱና ዋናው ጉዳይ ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን የሚገልፅበት እድል እየጠበበ መምጣቱ ነው፡፡ ስርአቱ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት ብቻ የሚመራ መሆኑና የህብረተሰቡ አስተሳሰብና ጥቅሞች የሚወከሉበት ም/ቤት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፓርላማ መጥፋቱ ሌላው ነው፡፡ ኢህአዴግ ስለ ዲሞክራሲ ሲያወራ ትርጉም የሌለው የታይታ ዲሞክራሲ እንደሆነ፣ የተለያዩ ሃሳቦችም ተቀባይነት እንደሌላቸው ህብረተሰቡ እየተረዳ ነው የመጣው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቀበሌ እስከ ፓርላማ ም/ቤቶች ጥርግርግ ብለው መውጣታቸው ህዝቡ ብሶቱን የሚተነፍስበት መድረክ አሳጥቶታል። ህዝቡ መድረኩን ሲያጣ ሊከተል የሚችለው አማራጭ አመፅንና ተቃውሞን ነው፡፡
ቀደም ሲል ይሄ አልታየም፤ ምክንያቱም ቢያንስ በርከት ያሉ ፕሬሶች ነበሩ፡፡ ተቃዋሚዎች በፓርላማ ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክሮች ይካሄዱ ነበር፡፡ ህዝባዊ ስብሰባዎችም ይደረጋሉ። በአጠቃላይ የተለያዩ የህብረተሰቡ ቅራኔዎችና ሃሳቦች የሚስተናገዱበት እድል ነበረ፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ወደ አመፅና ግጭት የመሄድ እድሉ እምብዛም ነበር፡፡ አሁን በሂደት ይሄ እየጠፋና መድረኩ እየጠበበ በመምጣቱና ፍፁማዊ የአንድ ፓርቲ የበላይነት በመንገሱ ለአመፅና ግጭቶች በር ከፍቷል፡፡ መንግስት ሰላማዊ ትግልንም ፈርቶ፣ የትጥቅ ትግልንም ፈርቶ መኖር አይችልም፡፡ አንዱን መምረጥ አለበት፡፡ የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነት የሚስተናገድበት መድረክ ከሌለ፣ አመፅና የትጥቅ ትግል ምቹ መደላድል እያገኘ እንደሚሄድ መታወቅ አለበት፡፡ የተፈጠረው ችግርም የዚህ ሁሉ መግለጫ ነው፡፡
አመፅና ግጭቶቹ የመብት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የብሄር አክራሪነት የታከለባቸው ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ህብረተሰቡ በታሪኩ አብሮ የኖረ ህብረተሰብ ነው፡፡ በልዩነት የመኖሩን ያህል ብዙ የአንድነት መገለጫ የሆኑ እሴቶች አሉት፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ግን ሲሰበክ የኖረው ልዩነቱ ነው እንጂ አንድነቱ አልነበረም፡፡ በዚህ ህብረተሰቡ “እኛና እነሱ” የሚል አመለካከት እንዲያዳብር ነው የተደረገው። ይሄ ሂደት ወደ ጠባብነትና ዘረኝነት የሚያመራ አደጋ እንደሚፈጥር ግልፅ ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ይሄን ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ሃገራዊ ራዕይ ሳይሆን አካባቢያዊ ሁኔታን ነው፡፡ እኛ ብሎ “እነሱ” የሚባሉትን የሚጠላ ኃይል ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡ በኔ ሀብት ማንም ሊጠቀም አይገባም ብሎ የሚያምን ህብረተሰብ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡
ጤናማ ያልሆነ ጥላቻ የታከለበት ፉክክር ነው እየዳበረ የመጣው፡፡ ስርአቱምኮ የጠባብነት ችግር እንዳለበት ይናገራል፡፡ ግን ይሄን የጠባብነት አመለካከት ወደዚህ ደረጃ ያጎለበተው ማን ሆነና ነው ዛሬ እሱ ወቃሽ የሆነው? አሁን እያጨድን ያለነው የዚህን ፍሬ ነው፡፡፡ ይሄ ሀገር ወዴት እየሄደ ነው ተብሎ ተገምግሞ መሰረታዊ ማሻሻያ መወሰድ ካልተቻለ አደገኛ ነው፡፡ በተሃድሶ ላይ በር የዘጋ ስርአት አመፅና አብዮት ነው የሚያስተናግደው፣ ይሄ በታሪክ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ሰላማዊና ህጋዊ መንገዱን ባጠበበ ቁጥር ሊያስተናግድ የሚገደደው አመፅና አብዮት ነው፡፡
ኢህአዴግ ያለፈውን ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል አደጋው ሊታየው ይገባ ነበር።  ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የብዙሃን አስተሳሰብ ተጨፍልቋል፡፡ አንድ አስተሳሰብ ብቻ የህብረተሰቡን ህይወት እየወሰነ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የብዙሃን አስተሳሰብና ፓርቲ ስርአት አስፍነናል ማለት በህዝብ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ኢህአዴግ በሌሎች ላይ ጣት መቀሰሩ የትም አያደርሰውም፤ ራሱን ነው መመርመር ያለበት፡፡ ተቀናቃኙም ሃይል ቢሆን አመፅና ግጭት ይህቺን ሀገር ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ብጥብጥ ኢትዮጵያን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳት ይችላል፡፡
መንግስት ችግሩን እያስተናገደ ያለበት ሁኔታ ያዋጣል ብለው ያስባሉ?
እንግዲህ ችግሩን ከህብረተሰቡ ጋር እየተወያየሁ እየፈታሁ ነው ይላል፡፡ በኛ ግምገማ ግን መንግስት በቀጥታ ከጉዳዩ ባለቤት ጋር ሲወያይ አይደለም የምናየው፤ የራሱን ካድሬዎች እየሰበሰበ ነው እያወያየ ያለው፡፡ የራሱን ካድሬዎች ያወያያል፤ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ይቀረፃል፤ ያ ለህዝብ ይቀርባል፡፡ ይሄ መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር አይሄድም፡፡ ህዝቡ የመንግስት ሚዲያዎችን በዚህ የተነሳ ማየት አይፈለግም፤ ሌሎች የውጭ አማራጮችን ይሻል። 25 ዓመት ሙሉ በሚዲያዎች እየተሰራ ያለው ፕሮፓጋንዳ፣ ስርአቱን በህዝብ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ ህዝብና መንግስትን ሆድና ጀርባ አድርጎታል፡፡ አሁን መንግስትን የሚያምን ህዝብ  የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው አመፅና የትጥቅ እንቅስቃሴዎች ካለፈው ጊዜ በተሻለ እድል እያገኙ የመጡት፡፡
ባለፉት 4 ወራት በተከሰቱ ግጭቶች የበርካቶች ህይወት መጥፋቱ ተገልጿል፡፡ እልባቱ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
በዚህ ጉዳይ ብዙ ድርድር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ እነ ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሶርያ… አሁን ያሉበት ችግር ውስጥ የገቡት ተሃድሶ ማካሄድ አቅቷቸው ነው፡፡ ስርአቶቹ ቆም ብለው ራሳቸውን ገምግመው፣ ተሃድሶ ማድረግ አቅቷቸው ነው አብዮት ተቀስቅሶ ለራሳቸውም ለህዝባቸውም የማይጠቅም ሁኔታ ውስጥ የገቡት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ቆም ብሎ ተሃድሶ የማያደርግ ከሆነ፣ እነሱ የደረሰባቸው እጣ ፈንታ በሱም ላይ የማይደርስበት ምክንያት የለም፡፡ ችግሩ ግን በመንግስት ላይ ደርሶ የሚቆም አይደለም፡፡ ለሀገርና ለህዝብ የሚተርፍ ነው፡፡ በተለይ በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ ቅራኔና የልዩነት ስፋት እንዲሁም ሲሰብክ ከኖረው የጠባብነት አስተሳሰብ አንፃር፣ በግብፅና በሊቢያ የተፈጠረው አይነት እዚህ ቢያጋጥም፣ የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከት ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ ቢከሰት የአደጋው ተጠቂ የሚሆነው መንግስት ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ተገቢ አይሆንም፡፡ መንግስት ይሄን አደጋ በሚገባ ተገንዝቦ ራሱን ለተሃድሶ ዝግጁ ማድረግ አለበት፡፡
ለተሃድሶ ዝግጁ መሆን አለበት ሲሉ ምን ማለት ነው?
ለዚህ ሀገር የታይታ ሳይሆን እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ የህብረተሰቡ የተለያዩ አመለካከቶች የሚወከሉበት መድረክ መፍጠር መቻል አለበት፣ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው፣ ልዩነታቸውንና ሃሳባቸውን የሚያራምዱበት ሁኔታ መኖር ይገባዋል፡፡ በየ5 ዓመቱ የሚካሄዱ ምርጫዎችም ይሄን የህብረተሰቡን የሀሳብ ልዩነት የሚያስተናግዱ መሆን አለባቸው፤ ለታይታ ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡ ግጭቱን በሃይል ለተወሰነ ጊዜ ማስቆም ይቻል ይሆናል፤ በዘላቂነት ግን ማስቆም አይቻልም፡፡ ዘላቂው መፍትሄ ከተፈለገ፣ ሃቀኛ የሆነ ተሃድሶ መምጣት አለበት፡፡
ሰሞኑን የታክሲ ሾፌሮች አዲሱን የመንገድ ደህንነት ደንብ በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፡፡ አድማው ተገቢ ነው ይላሉ?
የታክሲ ሹፌሮች ህይወታቸው የተመሰረተበት ስራ ስለሆነ ህጉ ሊያመጣባቸው የሚችለው ችግር ሊያሳስባቸው ይችላል፡፡ ሲያሳስባቸው ተቃውሞአቸውን ማቅረብ መብታቸው ነው፡፡ ይህን ማንም ሰው መቃወም ያለበት አይመስለኝም፡፡ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት በሰላማዊ መንገድ ነው። ስራ ማቆም አንድ የሰላማዊ ተቃውሞ መንገድ ነው። ታክሲዎች ሲቆሙ ዞሮ ዞሮ ህብረተሰቡ ይጎዳል፡፡ ስለዚህ ሹፌሮችና መንግስት ተወያይተው መፍትሄ ማበጀት አለባቸው፡፡ ግን በአጠቃላይ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል ወይም በሌሎች አካባቢዎች የሚነሱት ተቃውሞዎች መነሻ ምክንያቶች ይኑራቸው እንጂ ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተከሰተውም ይሄ ነው፡፡ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሻ እንጂ ዋነኛ ጥያቄዎች አይደሉም። በኦሮሚያ ያለው የማስተር ፕላን ጥያቄ ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፤ስረ መሰረቱን በደንብ መመርመር ያስፈልጋል፡፡
ለነዚህ ሁሉ የሀገሪቱ ችግሮች ምንድነው መፍትሄው ይላሉ ትሄ ያበጁለታል?
ህዝብና መንግስት እየተራራቁ እንደሆነ መንግስት ተገንዝቦ፣ ህዝቡ በአግባቡ ብሶቱንና ተቃውሞውን የሚያሰማበት መድረክ መፍቀድ አለበት፡፡ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች እድል የሚሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ አንዱ መፍትሄ ሰላማዊና ህጋዊ መንገዱን ማስፋት ነው፡፡ የብዙሃን ፓርቲ አሰራር ሰፍኖ ልዩነት፣ ብሶት፣ ተቃውሞ… የሚደመጥበት መድረክ ያስፈልጋል፣ አሁን ግን ይሄ የለም፤ የአንድ ፓርቲ ብቸኛ የበላይነትና ቁጥጥር ያለበት ሀገር ነው፡፡
ሁለተኛው ህገ-መንግስታችንን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የፌደራል አደረጃጀቱን በተመለከተ አደረጃጀቱ 25 ዓመት ውስጥ አንድነታችን እያጠናከረ መጣ ወይ? በህብረተሰቦች ዘንድ መተማመንን መፈቃቀርን ነው ወይ ያመጣው? የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ መሻሻል ካለበት መሻሻል አለበት፡፡ አሁን የሚደረገው ወታደራዊ እርምጃ ለጊዜው ችግሩን ሊያስታግሰው ይችላል ግን ያዳፍነዋል እንጂ አያጠፋውም፤መልሶ መፈንዳቱ አይቀርም፡፡

%d bloggers like this: