FOR BETTER OROMIA

ኦሮሞ እና ኦሮሚያ — የዓፄዎቹን ጋኔኖች ያናወጡ ታላላቅ ስሞች

ከጂቱ ለሚ*

እዉነትም ይህ ስም ታላቅ ነዉ። የዓፄዎቹ ጋኔኖችም ይህንን ያዉቁታል፥ ይፈሩታልም። መንፈሱ ባለበት ኣካባቢ ይህ ስም ከተጠራ ጋኔኖቹ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይንጫጫሉ፤ ይቆጣሉ፤ ተስፋ ሲቆርጡ ደግሞ እየተራገሙም ቢሆን ከነጭፍራዎቻቸዉ ጓዛቸዉን ነቅለዉ ወደ ጥልቁ ይገባሉ። ስሙ ከስም በላይ ይሆንባቸዋልና ሊቋቋሙት አይችሉም። ለሙከራ በየካፌዉ፣ በየሬስቶራንቱ አልያም ታክሲ ዉስጥ ስትገቡ ይህንን ስም ከፍ ባለ ድምጽ ብትጠሩ የጋኔን መዓት ሲደናበር ታዩታላችሁ። አልያም ደግሞ በእረፍት ቀናችሁ በኦሮሞ ባሕላዊ ልብስ ሽክ ብላችሁ በሰፈራችሁ ወይም በመዝናኛ ቦታዎች አካባቢ ጎርደድ-ጎርደድ በሉ። የሆነ ሰዉ ባልጠበቃችሁት መልኩ ጭር ጭር ብሎ በጥላቻ ዓይን ከተከተላችሁ ያ ጋኔን እየተቃጠለ ነዉና ዘና በሉ።

ከዓጼ ኃይለስላሤ ዘመነ-ንግሥና ጀምሮ መንፈሱ ከነገሠባቸዉ ሥፍራዎች የፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ ዋነኛ ሆኖ ነበር። እዚያዉ ቦታ ላይ ለመንፈሱ ሥርዓተ-ዓምልኮ ይፈጸማል። መስዋዕት ይቀርባል። ዉዳሤና ቅዳሤ ይቸራል። ጭፍራዎችና ደቀ-መዛሙርት ሰልጥነዉ፣ ተቀብተዉና ተጠምቀዉ ለመንፈሱ ሀዋርያነት ከበቁ በኋላ በየቦታዉ ይበተናሉ። አንድ ሀገርአንድ ሀይማኖትአንድ ቋንቋና አንድ ባሕል የመንፈሱ መሪ ቀኖናዎች ናቸው። ከዚህ ዉጪ ያሉ እዉነታዎችን አይቀበልም። በተለይ ደግሞ ኦሮሞ እና ኦሮሚያ የሚባሉ ስሞችን መስማት እንደ እሳት ይለበልበዋል። ለእኔና ለወገኖቼ ደግሞ ይህ ስም ከማር ይበልጥ ለኣንደበታችን ይጣፍጠልና በሄድንበት ቦታ ሁሉ ስለታላቅነቱ እንመሰክራለን። እዉነታዉንም እናስተምራልን። እዉነትን ይዞ ዝምታ አናዉቅበትምና “ዝም በሉ!” በተባልን ቁጥር ደግሞ ይብስብናል።

ከ1991ዱ ለዉጥ በኋላ የታየዉ የነባራዊ ሁኔታ መቀየር ለዓጼዎቹ ጋኔን ታላቅ ነዉጥ ሆነ። በጭራሽ ሊቋቋሙት የማይቻላቸዉ ይህ ታላቅ ስም አየሩን ጥሶ ገባ። ጋኔኑ መንፈሱ ተሸበረ። በወቅቱ ከባዕድ ቋንቋ ተጽዕኖ ተላቀዉ አፋቸዉን በፈቱበት ቋንቋ የመማር ዕድል ያገኙ ሕጻናት በደስታ ሲቦርቁ ያየ ይህ ክፉ መንፈስ በቅናት ተይዞ ያሰማ የነበረዉ ጫጨታ ቀላል አልነበረም። እናማ! አሁን ዉጊያዉ ጫጨታና ሁካታ ከማያቆመዉ ሠራዊት ጋር ሆኗልና ዓይኑ እያያ፣ ጆሮዉም እያሰማ ምድሪቷ ስለኦሮሞና ኦሮሚያ ትሰማለች። ሰማዩም ማዳመጡን ይቀጥላል። ግልጽ በሆነ ቋንቋ ደግሞ ዓይናቸዉ እያያ፣ ጆሮኣቸዉ እየሰማ ኦሮሚያ ነጻ ትወጣለች!

እዉነትን የሚጠላ፣ ሕዝቦችን ለዘለዓለም ጭለማ ዉስጥ ማቆየትን የሚሻ፣ የንጹሃንን ደም የሚጠጣ ክፉ ነገር ቢኖር ጋኔን (demon) ነዉና አንባቢዎቼ ተምሣሌታዊ አገላለጼን በዚሁ መልኩ ይረዱታል ብዬ አምናለሁ። አነሳሴ ትዉልዱ ከዚህ ክፉ አመለካከትና ተግባር ጋር የሚያደርገዉን ሁለገብ ትግል ብዙዎች ባላተኮሩበት አቅጣጫ መቃኘት ነዉና ወደዚያዉ ልዝለቅ።

አንድ ወቅት በፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙ የነጻነት ተፋላሚዎች መንፈሱን ያሸበረ ዘመቻ ኣዘጋጅተዉ ነበር። ዘመቻዉ በተቻለ መጠን መላዉን የፊንፊኔ ምድር ያካለለ ሲሆን የሕዝብ ማመላለሻ አዉቶቡሶች፣ ታክሲዎች፣ ሬስቶራንቶችና ካፌዎች፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚሸጡባቸዉ አደባበዮችና ባጠቃላይ መንፈሱ በብዛት የሚሰባሰብባቸዉ አካባቢዎች ላይ በተለይ ያተኩራል። በዘመቻዉ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በታሪክ ዕዉቀታቸዉ የመጠቁ፣ በፖላቲካ ኪሂሎታቸዉም የላቁ፣ የተደናገጠዉን መንፈስ ለማረጋጋትም በአካላዊ ብቃታቸዉ ጥንቁቅ የሆኑና በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ጥበብን የታጠቁ ስለሆነ መንፈሱ ሊቋቋማቸው አልደፈረም። ደግሞም አይቻለዉም ነበር።

ስለዚህም በዘመቻው መጀመሪያ አካባቢ መንፈሱ ተደናብሮ በየፌርማታዉ ላይ ያለቦታዉ ሲወርድ፣ በየሆቴሎቹና ሬስቶራንቱ ዉስጥ የቀረበዉን ምግብና መጠጥ ጥሎ ሲሸሽ ማየቱ አስገራሚ ትዕይንት ሆነ። ለሣምንታት በዘለቀዉ በዚህ ዓይነቱ ዘመቻ ስለኦሮሞና ኦሮሚያ ዕዉነታዎች ለጀማዉ በሰፊዉ ተሰብኳል። በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል። ከከረ-ቆሬ እስከ ከረ-አሎ፣ ከከረ-ቃሉ (ቃሊቲ) እስከ ከረ-ገፈርሳ ድረስ በአምስቱ የፊንፊኔ በሮች የነጻነት መልዕክተኞች ተመላልሰዋል። ለተገፉ ሕዝቦች የክብር ብርሃን ፈንጥቋል። ለዘመናት በመንፈሱ ተጽዕኖ ሥር የወደቁ ወገኖች ነጻ ወተዋል። የተነጠቁትን ብሔራዊ ኩራታቸዉን መልሰዉ ተላብሰዋል። በኣንጻሩ ደግሞ ለዘመናት የበላይነትን ይዞ ሲፏልል የኖረ ዉሸታም መንፋስ ከነቀንበሩ ወደ ጥልቁ ተጥሏል። በሦስት ሺዎች ዓመታት ያሰላ የነበረ ዘመኑ አግባባዊ በሆነ የታሪክ መስፈሪያ ተለክቶ ባይመቸዉም ተገቢ ቁመቱን አግኝቷል።

በሌላ መልኩ ተመሳሳይ ዘመቻ ስለመኖሩ የተረዳሁት በቃሊቲ እሥር ቤት ዉስጥ ነበር። በፊንፊኔና ዙሪያዋ የሚኖረዉ የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት የተቀነባበረ ሤራዎች ሰለባ ሆኖ ቆይቷል። ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር በሚፈራረቁ የዘመኑ ጉልተኞች ከቤት-ንብረቱ ይፈናቀላል። ማህበራዊ ሕይዋቱ ይናጋል። በኣካባቢዉ ላይ የነበረዉ አሻራዉ ይፋቃል። ይህ ስልታዊ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ዛሬ የመጨረሻ ምዕራፉን እንደያዘ በቅርቡ የታወጀዉ ማስተር ፕላን እንድምታ አመላካች ነዉ።

ይህ ዓይነቱን ኣደጋ ለመቋቋም የአቅማቸዉን ያህል ደፋ ቀና ሲሉ የተገኙ የአካባቢዉ ወጣቶችን ለማዳከም በየጊዜዉ የተለያዩ የማጥመጃ አንቀጾች ይዘጋጃሉ።ኣንዴ በአደገኛ ቦዘኔነት በሌላ ጊዜ ደግም ሌላ የፈጠራ ክስ እየተፈለገ ወራንት ይቆረጥላቸዉና መዳረሻቸዉ ወህኒ ቤት ይሆናል። በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ወደ እስር ቤቱ የሚወረወረዉ ወጣት ቁጥር ቀላል አይደለም።

ይህንን ወጣት በኣንዴ ወደ ብሔራዊ ትግል ማምጣቱ ከባድ ቢሆንም በተገኘ አጋጣሚ ብሔራዊ ንቃቸዉን በማጎልበት ወደ ነጻነት ትግሉ መሳብ እንደሚቻል ግን አይተናል። ይህንን እዉነታ በተግበር ያረጋገጡ የቃሊቲ ወገኖቼን ምንጊዜም በኩራት አስታዉሳቸዋለሁ። በዚያ እጅግ ተፈታታኝ የሕይዋት ጎዳና ላይ ሰዉ ከራሱ ኣልፎ ለሕዝቡ ያስባል ብሎ መገመት በሚያስቸግር ሁናቴ ዉስጥ የቃሊቲዉ ዘመቻ እዉን ሆነ።

በዚህ ዘመቻ በፈጠራ ክስ ወደ ወህኒ የሚገቡትን ወጣቶች ብሔራዊ ማንነታቸዉን በማጎልበት የነጻነት ታጋዮች እስከ መሆን ድረስ አብቅቷቸዋል። በሂደቱ የኦሮሞን ባንዲራ በክንዱ ላይ አስሮ የሚንጎማለል ቆራጥና ደፋር ወጣት ማፍራት ተችሎ ነበር። በወቅቱ ይህንን የተመለከቱ የእስርቤቱ ሹሞች (አፈወርቅ ተፈራ፣ ፍሰሃ ገ/ማሪያምና ኢያሱ) በሁኔታዉ ተደናግጠዉ “… በተራ ወንጀል የሚናስረዉ ወጣት ቀንደኛ ኦነግ እየሆነ ይወጣል።” በማለት ስጋታቸዉን ገልጠዋል። በነገራችን ላይ እነዚህ የእስር ቤት ኃላፊ የነበሩ ሰዎች በኦሮሞ እስረኞች ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽሙ የነበሩ መሆናቸዉን በዚሁ አጋጣሚ ወገኖቼን ማስታወስ እወዳለሁ።

በአነጻጻሪ ገለጻ የተጀመረዉ ሀሳቤን ማሰሪያ ላብጅለት። የኦሮሞ ሕዝብ የነጻነት ትግልና ታጋዮች ከእንግዲህ ወዲህ በሁኔታና በቦታ አይወስኑም። ሰፊ አድማስን፣ ብርቱ መሠረትን ማካለል ችለዋልና። ከአሁን በኋላ የትግላችን ቀስት ካልተጠበቀ አቅጣጫና ባልተገመተ ፍጥነት በጠላት ልብ ላይ ያነጣጥራል፥ ጭፍሮቻቸውንና የእኩይ መንፈስ ማህደራቸዋንም እስከወዲያኛው ያፈርሳል። የትግላችን ስልትም እንዲሁ ጠላት ከለመደዉና ከሚጠብቀዉ ቀመርና ሥሌት ዉጭ አደናጋሪና አደናባሪ ይሆንበታል። የሃገሬ ሕዝብና ምድር ብቻ ሳይሆን የሃገሬ ሰማይና ዳመናም ነጻነትን ኣሽቷልና ይህ በፍጥነት እዉን ይሆናል። ያቀን በመቃረቡ እነሆ የምሥራች ዜማ ከአሁኑ በአንደበታችን ተቀምጧል – ዓይናቸዉ እያያ፣ ጆሮኣቸዉም እየሰማ ኦሮሚያ ነጻ ትወጣለች!

* ጂቱ ለሚ ነኝ

በቸር ያገናኛን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: