FOR BETTER OROMIA

የነገሮ   ዋቅጅራ ታሪክ በጎጃም (1864-1917)

(Oromedia, 1/04/2014)  ዶ/ር ሥርግው ገላው በመጽሐፋቸው መግቢያ  ላይ እንደሚጠቅሱትና አድማሱ ጀምበሬም  በመጽሐፈ ቅኔያቸው 1963 ላይ እንዳሰፈሩት፤  አለቃ ተክለ ኢየሱስ የመጀመሪያ ስማቸው ነገሮ  ነው፤ አባታቸው ዋቅጅራ፣ እናታቸው ገላኔ ይባላሉ።  ተክለ ኢየሱስ በ1871 ዓ.ም የ7 ዓመት ልጅ ነበርኩ  ብለው ስለጻፉ በ1864 ዓ.ም አካባቢ ኩታይ ውስጥ  እንደተወለዱ ይገመታል፡፡

በዶ/ር ሥርግው ገላው ሐተታ መሠረት፤ ራስ  አዳል ተሰማ (በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) ወደ  ኩታይ የዛሬዋ ምሥራቅ ወለጋ ዘምተው አቡናንና  አዋጠን ባቀኑበት ወቅት አጎታቸው የሌምቱ ጎሹ  የዘመቻቸው ተካፋይ ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት የሌምቱ  ጎሹ 8 ሕፃናትን ከኩታይ ይዘው ወደ ሀገራቸው  ደብረ ድሙና (ጎጃም) ተመለሱ፡፡ ሕፃናቱም አጋ፣  ደንገላ፣ ፈይሳ፣ ዋቅጅራ፣ ወቅኬኒ፣ ጅራታ፣ አገሾ፣  ነገሮ ይባላሉ፡፡ ከተጠቀሱት ሕፃናት ውስጥ ነገሮ  በኋላ ተክለ ኢየሱስ የተባሉት የዚህ ታሪክ ጸሐፊ  ናቸው፡፡

የአለቃ ተክለ ኢየሱስ ታሪክም ልክ የታላቁ  አሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ አያት አብርሃም ሀኒባል በሩሲያ ንጉሠ ነገሥት፤ በቀዳማዊ ጴጥሮስ ቤተ መንግሥት ሞገስ አግኝቶ እንደነበረ ሁሉ አለቃ ተክሌም በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት እንደነበራቸው ወደፊት እንመለከታለን። የንጉሥ ተክለሃይማኖት አስተሳሰቡም በእውቀት እንጂ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ማጤን ይገባል፡፡

ሕፃናቱ እንደየዕድላቸው በተለያየ ሙያ ሲሰማሩ፣ ነገሮ በመጀመሪያ የወንድ እልፍኝ ገበታ አቃፊ ሆኑ፡፡ አማርኛ ሲለምዱ ክርስትና ተነሥተው ዲማ አባ ሣህሉ ከተባሉ መምህር ዘንድ ገብተው የቤተክህነት ትምህርት ተማሩ፡፡ በብልህነታቸውና በአስተዋይነታቸው አሳዳጊያቸው የሊምቱ ጎሹ በእጅጉ ይደነቁ ነበርና የመሞቻ ጊዜያቸው ሲደርስ፣ ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ስኂን ተክለ ኢየሱስንና ወልደሰንበትን አደራ ሰጥቼሻለሁና እንደልጆቻችን አርገሽ አሳድጊልኝ ብለዋቸዋል፡፡ ባለቤታቸውም  አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ ቀድሞ ጅራታ ይባሉ የነበሩት ወልደ ሰንበት፤ ደብረ ጽሙና ተምረው የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን (ቄስ) ሆነዋል፡፡ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ እንዲሁ ቅኔን ጨምሮ የቤተ ክህነቱን ትምህርት በሚገባ ተምረው የታወቁ ሠዓሊና ታሪክ ጸሐፊ ሆነዋል፡፡ በዲቁና ማዕረግም የገናዚ ማርያምን አገልግለዋል፡፡ በ1881 ዓ.ም ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ለመገናኘት ወደ ቤጌምድር ሲሔዱ፣ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራም ለምኒልክ የሥዕል በረከት ይዘው ከተክለ ሃይማኖት ሠራዊት ጋር ወደ ቋና ተጉዘዋል፡፡ ቋና ላይ አየለ ወሰን በተባሉ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የእልፍኝ አሽከር አነሳሽነት ለንጉሥ ምኒልክ የተሣለውን የሥዕል ገጸ በረከት አለቃ ተክለ ኢየሱስ ለንጉሥ ተክለሃይማኖት አበረከቱ፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም በረከቱን ተቀብለው ደመወዝ ቆረጡላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ መደበኛ ሥራቸው ሥዕል ሆነ፡፡ የተዋጣላቸው ሠዓሊ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ በሥዕል ሙያቸው የዲማ ጊዮርጊስን፣ የደብረ ማርቆስን፣ የደብረ ዘይትን፣ ማርያምን፣ የጠያሜን፣ የጣማዊትን፣ የድልማ አማኑኤልን አብያተክርስቲያናት አስጊጠዋቸዋል፡፡ የደብረ ማርቆስን መጽሐፈ ወንጌል፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ቤተ መንግሥትና የራስ ኃይሉን መኖሪያ ቤት በሥዕል አሸብርቀዋቸዋል፡፡ የሥዕል ትሩፋቶቻቸው በአሁኑ ሰዓት ሕያው ምሥክር ሆነው በየቤተክርስቲያኖቹ ውስጥ ይታያሉ፡፡ እኒህ ሊቅ በዘመኑ ደረጃቸውም በጎጃም ከተከበሩ ሰዎች ተርታ ስለነበር ማኅበራዊ ከበሬታ ነበራቸው፡፡ የቤተ መንግሥት መጠጫቸው በንጉሥ ተክለሃይማኖት የተበረከተ ሲሆን “ዝ ኮልባ ዘአለቃ ተክሌ ዘወሀቦ ንጉሥ ተክለሃይማኖት” ይላል፡፡ ትርጉሙም “ይህን የወይን ጠጅ መጠጫ ለተክለ ኢየሱስ የሰጠው ንጉሥ ተክለሃይማኖት ነው” የሚል ነው፡፡

ለእኒህ ጥበበኛ ሰው በጊዜው በነበረው የመተዳደሪያ ስሌት መሠረት በወር ከሚከፈላቸው አምስት ማድጋ እህልና አምስት ጠገራ ብር ሌላ በየወሩ ከሚያስተዳድሩዋት ከጥድ ማርያምና ከማቻከል የአጤ ቆሎ እህል እየተሰፈረ ይገባላቸው ነበር፡፡ እንዲሁም ከግራ ቅዳምንና ከአጫሙስ ገበያ በወር በወር በገፈፋ ቀረጥ ይገባላቸው ነበር፡፡ በንጉሡ ፈቃድ የንጉሡን ልጅ የራስ በዛብህ ሚስት የነበረችውን የወ/ሮ ተዋበች ታውቄን ልጅ ዓለሚቱ መርሻን እንዲያገቡ መደረጉ በደ/ማርቆስ ቤተ መንግሥት የነበራቸውን ማኅበራዊ ከበሬታ ያመለክታል፡፡ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ወ/ሮ ዓለሚቱ መርሻን ሲያገቡ ንጉሡ አምስት ቁም ከብትና ሦስት አገልጋዮችን ጨምረው ሸልመዋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘመን፣ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ በደስታ ቢኖሩም ንጉሡ ከሞቱ በኋላ ግን አስቸጋሪ ሕይወት መርተዋል፡፡ ይኸውም በራስ ኃይሉ ተንኮል (በጊዜው ደጃች ሥዩም ይባሉ ነበር) ፈቃድ የሌለው ማኅተም እንዲቀርፁ ስለተደረገ በዚህ ተወንጅለው ደጃች ስዩምም ከሥልጣናቸው ተሽረው ወደ አፍቀራ (ሸዋ) ሲጋዙ፣ አለቃ ተክለ ኢየሱስም በዓፄ ምኒልክ ትእዛዝ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ወኅኒ ወረዱ፡፡ በመጨረሻ በእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ አሳሳቢነትና በእቴጌ ጣይቱ አማላጅነት ብዙ ሳይታሰሩ ተፈትተዋል፡፡ እቴጌይቱም የሥዕል ችሎታቸውን በመገንዘባቸው ጉራምባ ማርያምን እንዲስሉላቸው በየቀኑ ድግስ እንዲደገስላቸው ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ ሦስት ዳውላ እህል ሁለት ቁንዶ በርበሬ፣ ማር፣ አንድ ሙክት፣ ለአሥር ቀን አምስት ኩባያ አሻቦና አንድ ዕቃ ቅቤ በየወሩ ደመወዝ ቆርጠውላቸው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሸዋን ብዙም አልወደዱትም፡፡ የአዛዥ አማኑኤልን ተንኮል ለመቋቋም አቃታቸው፡፡ በዚህ ላይ ዓይናቸውን ታምመው ለመዳን ተቸገሩ፡፡ ዓይናቸውን በማስታመም ላይ እያሉ ደግሞ ሌላ ችግር ተፈጠረባቸው፡፡ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቀጣሪነት ያገቧቸው ሚስታቸው ወ/ሮ ዓለሚቱ መርሻ

“አንተም እንዳትመጣ እስርኛ ነህ ባሌ፣

እኔም እንዳልመጣ ሸዋ አይደለም ክፍሌ፣

ቶሎ ፍታኝና ፈጽሞ ልቅርብህ፣

የከብቴንም ድርሻ እንድትሰጠኝ ከፍለህ”

የሚል ደብዳቤ ኩላቸው፡፡ ከዓይናቸው ሕመም ይልቅ አለቃ ተክሌን ይኸ በጣም አሠቃያቸው፡፡ ዓፄ ምኒልክን አስፈቅደው ወደ ጎጃም ተመለሱ፡፡ ዐባይን ተሻግረው ኅዳር 30 ቀን 1895 ዓ.ም ደብረ ማርቆስ ቢደርሱም ባለቤታቸውን ወ/ሮ ዓለሚቱ መርሻን አላገኙዋቸውም፡፡ ይኸውም ከፍርሐት የተነሣ ዳሞት ከራስ መንገሻ አቲከም ግዛት ተደብቀው ስለነበር ነው፡፡

ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ወደ ጎጃም በተመለሱበት ወቅት የወቅቱ የጎጃም ገዥ ራስ በዛብህ ተክለሃይማኖት ሹም ሽር ሲያደርጉ፣ አለቃ ተክሌን የወንድማቸው የራስ ሥዩም (ኃይሉ) ወዳጅ ነው በሚል ስለአልሾሙዋቸው በመናደድ እንደገና ወደማይፈልጉት አገር ወደ ሸዋ ሊመጡ ሲሉ በመኳንንቱ ምክር ከጨሊያ እስከ ሟጨራ፣ የአዋባልን ሊቀካህናትነት ከነገደ በረከቱ ተሾሙ፡፡ ጣባ ኖላዊንም ተሹመው አስተዳድረዋል፡፡ከንጉሥ ተክለሃይማኖት ሞት በኋላ ብዙም ያልደላቸው አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ከመደበኛ የሥዕል ሥራቸው ሌላ የጎጃምን ታሪክ፣ የጎጃምን ትውልድና ካርታ በማዘጋጀት የደከሙ ጥበበኛ ናቸው፡፡

ይህንን ሁሉ የሠሩት በፈቃደ እግዚአብሔር እንጂ ዋጋ ተከፍሏቸው አይደለም፡፡ ለጎጃም በነበራቸው ቀናዒነት እንጂ፡፡ ቀናዒነታቸውንም ከጽሑፋቸው ጭምር ለመረዳት ይቻላል፡፡ አለቃ ተክሌ በመጨረሻ ዘመናቸው ባለቤታቸውን መፍታታቸው ሲያሳዝናቸው፣ በተለይ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አገልጋይ እንድትሆናቸው የሰጡዋቸው ሴት አገልጋያቸው በ1916 ዓ.ም ስለሞቱባቸው በእጅጉ አዝነዋል፡፡ ሴትዬይቱ (በስም አሰራኝ ቤት ተክለ ሃይማኖት) ይባላሉ፡፡ አሽከሪቱ ጠባያምና ግብረ መልካም ስለነበሩ በእርሳቸው ሞት አለቃ ተክሌ በእጅጉ ሲያዝኑና ሲተክዙ ቆይተው በግምት በ1917 ዓ.ም እዚያው ደብረማርቆስ እንዳረፉ ይገመታል፡፡ ዲያቆን ኅሩይ ተክሌ የተባለ ልጅ እንደነበራቸውም ተመልክቷል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: