FOR BETTER OROMIA

የኦሮሚያ ደራስያን ማህበር (OWA)

By Gadaa Ghebreab*

በውጭ አገር የሚገኙ መፅሃፍ ያሳተሙ ኦሮሞዎች OWA (Oromia writers Association) ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሰሞኑን ወሬ ሰማሁ። አሳቡን አልጠላሁትም። በርግጥ “የአፍሪቃ ቀንድ ደራስያን ማህበር” ቢሆን ይመረጥ ነበር። ትልቁ ጃንጥላ እስኪዘረጋ አነስተኛዎቹን መጠቀም ግን ክፋት የለውም። የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የአማርኛ ፀሃፊዎችን ብቻ የሚያገለግልና የሚያበረታታ በመሆኑ የOWA መቋቋም አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። እዚህ ላይ ግን በጥብቅ ማንሳት የምፈልገው አሳብ አለ። ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እና ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ እንደ ቀዳሚ የኦሮሚያ ፀሃፊዎች መጠን ስማቸውና ስራቸው በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ መካተት ይኖርበታል።

ፀጋዬና በአሉ ጊዜው በሚፈቅድላቸው መጠን ለኦሮሞ ህዝብ አርነት በብእራቸው ታግለዋል።በቀጭን መስመርም ቢሆን መልእክታቸውን ለማስተላለፍ ሞክረዋል። ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህን “አዋሽ” በሚል ርእስ የፃፈው ግጥም ለኦሮሞ ህዝብ አርነት ታጋዮች መሆኑ ይታመናል። የአዋሽን ግጥም መታሰቢያነት ለጋማቹ ቃማሊቲ ነበር የሰጠው። አበሾች “ጋማቹ” ማለት ስለማይችሉ “ገመቹ” ይላሉ። “ቃማሊቲ” ቃሉ ኦሮምኛ ሲሆን፣ ትርጉሙ “ጦጣው” ማለት ነው። ጋማቹ ማን እንደሆነ ፀጋዬ አልነገረንም። ምናልባት እንደ አብሼ ገርባ ወይም እንደ አገሪ ቱሉ የአርነት ትግል ጀምሮ በአጭሩ የተቀጨ ታጋይ ሳይሆን አይቀርም። ጋማቹ ቃማሊቲ ማን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ አጠያይቄ ሳይሳካልኝ ቀርቶአል።

የሎሬት ፀጋዬን የ”አዋሽ” መልእክት በትክክል ለመረዳት “አዋሽ” የሚለውን ቃል “ኦሮሞ” በሚል በመተካት መረዳትን ይጠይቃል። የቀዌሳ የልጅ ልጅ ፀጋዬ የኦሮሞን ህዝብ የነፃነት ጥያቄ በቅኔዎቹ ያንጎራጎረ የመጀመሪያው የአማርኛ ቋንቋ ባለቅኔ ነው። በመቀጠል የኦሮሞን ህዝብ የአርነት ጥያቄ የነካካው ዝነኛው ደራሲ በአሉ ግርማ ነበር። በአሉ ግርማ “ካድማስ ባሻገር” በሚለው መፅሃፉ እና “ኦሮማይ” ላይ ሁለት ገፀባህርያትን በመሳል የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ አንስቶአል። በአሉ ግርማ “ካድማስ ባሻገር” በተባለ መፅሃፉ ጫልቱ የተባለች ዋና ገፀባህሪ አስተዋውቆናል። ስሟን ሉሊት ታደሰ ብላ ቀይራ ትታያለች። ሞታ በተቀበረችው በቀድሞይቱ የኢትዮጵያ ኤምፓየር ውስጥ፣ “ጫልቱ” በሚል ስም መኖር ስለማይቻል ስሟን መቀየሯን አበራ ለተባለ ጓደኛዋ በምስጢር ታጫውተዋለች። ያም ሆኖ መፅሃፉ ሲያልቅ አበራና ሉሊት ጋብቻ ለመፈፀም አይበቁም። አበራ ወርቁ እስርቤት ገባ። “ጫልቱ እንደ ሉሊት” ህይወቷን ቀጠለች። በአሉ ግርማ በመቀጠል፣“ኦሮማይ” ላይ ታደሰ ቆሪቾ የተባለ ገፀባህርይ ይዞ መጣ። ሉሊት (ጫልቱ) የአባቷ ስም ታደሰ ነበር። የኦሮማይ ገፀባህርይ ታደሰ ቆሪቾ (የሉሊት አባት?) OLF ሆኖ መጣ። የቆሪቾ ወንድ ልጅ ከደርግ የመሳሪያ ግምጃ ቤት ጠመንጃና ሽጉጦችን“ለጠላት” የማሸጋገር ስራ ይሰራ ነበር። “ታደሰ ቆሪቾ መሳሪያ ያሸጋገረው ለማነው?” የሚል ጥያቄ የግድ ይነሳል። ለOLF ካልሆነ ለማን ሊሆን ይችላል?

ሎሬት ፀጋዬ በወቅቱየኦሮሞን ህዝብ የአርነት ጥያቄ በቅኔ ለመግለፅ እንደሞከረ ይሰማኛል። “እሳት ወይ አበባ” በሚል ርእስ በታተመው ጥልቅ ባህር በሆነው የስነግጥም መድበሉ ውስጥ ፀጋዬ፣ “አዋሽ” ሲል የገለፀው የኦሮሞን ህዝብ ትግል ይመስላል። ፀጋዬ በድምፁ “አዋሽ”ን ባነበበ ጊዜም አዋሽ እንደ ሩስያው ዶን፣ እንደ እንግሊዙ ቴምስ ወንዞች የህዝብ ምሳሌ መሆኑን በአንደበቱ ተናግሮአል። ዞረም ቀረ ተደራስያን ጥበባዊ መፃህፍትን በራሳቸው መንገድ የመረዳት መብት ያላቸው እንደመሆኑ “አዋሽ” ለኔ እንደ ገባኝ ያህል አቅርቤዋለሁ።

አዋሽ ወንዝሕዝብን ወክሎ እንደተፃፈ ፀጋዬ ደጋግሞ ገልፆአል። ግጥሙ የተፃፈው በግእዝ አቆጣጠር 1964 መሆኑሲታሰብ፣ የአዋሽ ገፀባህርያት ኦሮሞዎች መሆናቸው ሲመዘን፣ ፀጋዬከመጫና ቱለማ ማህበር ምስረታ ጋር አስታኮ አዋሽን እንደፃፈ ማሽተት እንችላለን። እንዲህ ይላል ሎሬት ፀጋዬ፣

አዋሽ ቡርቃው – መጫ ምንጩ
ዳዳ ፅንሱ፣ ሸዋ ፍንጩ
የንዳዱ የበረሃ እጩ
አዋሽየመጫ ስር ፍሳሽ
የዳዳ የቱለማ ደም
በረሃ እምትደመደም?

መጫ ቋጥሮ፣ ሸዋ ፀንሶ፣ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ፣ አሩሲ እምብርት፣ ከነቅሪቱ ተጉዞ
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን፣ አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ ማታሃራ፣ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ

ከዚያም ፀጋዬ አዋሽን እያሞገሰ መልሶ በምሬት ይወቅሰዋል።“አሸዋ” እና “በረሃ” እያለ የሚጠቅሰው የኦሮሞን ህዝብ አፍኖ በመበዝበዝ ላይ የነበረውን፣ በቀላድና በገባር ስርአት ጠፍንጎ በወቅቱ የኦሮሞን ህዝብ ባርያ አድርጎ በመግዛት ላይ የነበረውን የአማራ ገዢ መደብ ይመስላል። በቀጥታ አነጋገር የኦሮሞ ህዝብ ሰፊ ቁጥር ይዞ ሳለ፣ የጀግኖች መፍለቂያ ሆኖ ሳለ፣ በአናሳዎች ታፍኖ መበዝበዙን በማንሳት ፀጋዬ ምሬቱን በቅኔዎቹ ያዥጎደጉደዋል።እንዲህ እያለ፣

እስከመቼ ይሆን አዋሽ?
አሸዋ ለአሸዋ ድኸህ
ውስጥ ለውስጥ ምሰህ ጠልቀህ

አዋሽ ዘለአለምክን ፈስሰህ ባታልቅ
ምነው ተስፋ መቁረጥ አታውቅ?

እስከ መቼ ይሆን አዋሽ?
አዋሽ በቃኝ አትል ቆራጥ
ማን ያስተማረህ ፈሊጥ ነው፣ አረህ ለማለምለም መዋጥ?
አሻቅበህ ወደ ምስራቅ፣ ወደ ጀምበር መውጫ መናጥ?

አዋሽ ቡቡ፣ ሮሮ ብርቁ
የዘልአለም ንዳድ ስንቁ
አዋሽ አባ ብቻ ጉዞ
ዘልአለም ብሶት አርግዞ

እነ ዋቤ ሸበሌማ ሰብረው ውቅያኖስ ሲዘልቁ
እነ ግዮን ወርደው አልፈው ሱዳንን ምስርን ሲያጠምቁ
ምነው ያንተ ጉዞ ብቻ በረሃ ላይ መታነቁ?

እስከ መቼ ይሆን አዋሽ፣ ወዝክን አሸዋ ሲውጥህ
ደምክን በረሃ ሲመጥህ
ዘልአለም ሲመዘምዝህ?
እስቲ አንዴ እንኳ እንደነዋቤ፣ ባክህ ሂድ ውቅያኖስ ግባ
ዘለአለም በአሸዋ ሆድ ተውጠህ ከምታነባ

ቆራጡ እንኳ አንተ ነበርክ፣ የጀግኖች መፍለቂያ ኩሬ
የሰንጋ ፈረሰኞቹ፣ የነኦርዶፋ ጨንገሬ
የስንቱ መጠጊያ ዋሻ፣ አዋሽ ደኔ አዋሽ ዱሬ
የጥንተ ፍጡራን መደብ፣የቅድመ ማልካ ካንቱሬ

የኦሮሞ ህዝብ በተለይ ከአጤ ምኒልክ ስርአት ወዲህ በነፍጠኛው ስርአት ተወሮ የደረሰበትን አፈናና በደል ፀጋዬ በግልፅ አስቀምጦታል። የኦሮሞን ህዝብ “ተገድለህ ተጨፍጭፈህ የማታልቅ፣ ተስፋ የማትቆርጥ” ብሎታል። የኦሮሞ ህዝብ በህዝብ ብዛቱና ብቃቱ ቀዳሚ ሆኖ ሳለ፣ ጥያቄውም ተገቢና እውነት ሆኖ ሳለ፣ ዘልአለም የባእዳን ተገዢ በመሆኑ ፀጋዬ ተቆጭቶ ወቅሶታል። ኦሮሞዎች የገዛ ወገናቸውን ለመጨፍጨፍ የሌሎች መሳሪያ መሆናቸውን ፀጋዬ አንስቶ ተብከንክኖአል።“መጨፍጨፉ፣ መታፈኑ አይበቃህም ወይ? በቃኝ አትልም ወይ?” ሲል የኦሮሞን ህዝብ ጠይቆታል።

አዋሽ በቃኝን አታውቅም?
በምድር ማህፀን ከአድማስ አድማስ ዘለአለምክን ስታዘግም?
ወርደህ ሟጠህ ተንጠፍጥፈህ፣ አሜን ታከተኝ አትልም?

አዋሽ … የመጫ ቱለማ ደም ፍሳሽ…
ካገር ወዲያ ሞት ላትሞት፣ ካገር ምጥ ወዲያ ላታምጥ
እስከመቼ ይሆን አዋሽ ራስክን በራስህ እምትውጥ?

እስከ መቼ ይሆን አዋሽ – አዋሽ አባ ቡቡ ብሶት
የሰው ችግር ሳይደርስብህ፣ ሳይቸግርህ የእውነት እጦት?
ላትዘልቀው ላያዘልቅህ፣ ለማንም የትም እምትሞት?
እስከመቼ ይሆን “ኦሮሞ?”
ወዝክን አሸዋ እሚውጥህ
ደምክን በረሃ እሚመጥህ?
አጥንትህን ምድረበዳ፣ ሃሩር እሚመዘምዝህ?

እስከመቼ ይሆን አዋሽ?
ተስፋ መቁረጥን እማታውቅ?
ፈስሰህ ተሟጠህ እማታልቅ?

ሎሬት ፀጋዬ የኦሮሞን ህዝብ አምርሮ የወቀሰው ራሱን ከተጠያቂነት ገለል አድርጎ አልነበረም። “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” በተሰኘ ግጥሙ ራሱንም አፈር ያበላዋል።ሎሬት ፀጋዬ ራሱን ከአማራው ገዢ መደብ ቤተሰብ ውስጥ ቀላቅሎ የኦሮሞን ህዝብ እንደከዳ በግልፅ ቋንቋ ነበር ያስቀመጠው። ፀጋዬ ራሱን ከአማራው ገዢ መደብ ጉያ መጨመሩን እንደ ሃጢአት ቆጥሮ “ሰይጥኛለሁ” (ሰይጣን ሆኛለሁ) ሲል ነበር የገለፀው፣

አቴቴ ዱብራ ቦረና – አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
ምንም ቢርቅ ምንም ቢሸሽ፣ ህልሜ ከህልምሽ ተዛሞ
በአይንሽና በአይኔ መሃል፣ የሃሰት ስልጣኔ ቆሞ
ባንተያይ ባንወያይ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
እንደ ልጅነት ሰመመን፣ ለካስ እድሜም ያማል ከርሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፣ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ
በህልም ጣቶችሽ ሳቢኝ
መቸም በውን አልሆንሽም፣ እንዲያው በሰመመን ዳሺኝ
የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም
የኔ ክንድ ተልም አይተልምም
የኔ ጣት አረም አይነቅልም
በፊደል መፈደል በቀር፣ ጉልጓሎ እኮ አይጎለጉልም
ለስልሻለሁ፣ ሰልጥኛለሁ፣ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም።

አቴቴ ዱብራ ቦረና
መቼም ሁሉን ቻይ ነሽና
አጥንቴ ከአጥንትሽ ማእድን፣ ቢመነጭም ተቀምሞ
ከ“ሃና” ከ“አሃዱ” በፊት ከቃል በፊት አስቀድሞ
ዛሬ በአይንሽ በአይኔ መሃል፣ አጉል ስልጣኔ ቆሞ
ሰየጠንኩና አልሆንሽ አልኩ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ

በአሉ ግርማ እና ፀጋዬ ገብረመድህን ጊዜው በሚፈቅድላቸው መጠን የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ለመነካካት መሞከራቸው ያስመሰግናቸዋል። ያቅማቸውን ያህል በመሞከራቸው እንደ ትግል ጀማሪዎቹ እንደ ባሮ ቱምሳ እና ማሞ መዘምር፣ እንደነ ጄኔራል ታደሰ ብሩና አለሙ ቂጤሳ፣ በአሉና ፀጋዬም ስማቸው ሊዘከር ይገባዋል። OWA (የኦሮሚያ ደራስያን ማህበር) ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦለት፣ የትርጉም ስራ ሊሰሩ የሚችሉ ወጣቶችን አሰባስቦ በሺዎች የሚቆጠሩ መፃህፍትን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ያስተረጉማል፣ ያሳትማልም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

*Gadaa Ghebreab, www.tgindex.blogspot.com የቅዳሜማስታወሻ  can be reached at Email: ttgebreab@gmail.com

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: