FOR BETTER OROMIA

አብደላ ሶሬሳ – የቀድሞው የመኢገማ ሊቀመንበር

Abdallaa Soressaa694ከበደሌ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሀናቦሶቂ በተሰኘ አካባቢ የተወለዱት በ1930 ዓ.ም. ነበር፡፡ በግብርና ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተገኙት አቶ አብደላ ሶሬሳ ዕድሜያቸው ለትምህርት እስኪበቃ ድረስ በእረኝነትና በሌሎች መሰል ሥራዎች ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ በኋላም በአካባቢው ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ለመማር ብዙ ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ ትምህርት ከቅንጦት ይቆጠር ስለነበር እንኳንስ በገጠር ይኖሩ ለነበሩት አቶ አብደላ ለከተሜዎች የማይታሰብ ነበር፡፡

ለትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጡት ወላጅ አባታቸው ግን አቶ አብደላ እንዲማሩላቸው ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በከተማው የሚገኘው ብቸኛው ትምህርት ቤት ከሚኖሩበት አካባቢ 20 ኪሎ ሜትር ይርቅ ስለነበር እየተመላለሱ ለመማር አስቸጋሪ ነበር፡፡ ስለዚህም ሌላ ዘዴ መዘየድ ነበረባቸው፡፡ ተመሳሳይ ፍላጐት ካላቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በአካባቢው የሚገኙ ታዳጊዎች ፊደል መቁጠር የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡ በአካባቢው የቄስ ትምህርት ለማስጀመርም ተስማሙ፡፡ ይህም ግን ቀላል አልነበረም፡፡ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ሙስሊሞች ስለነበሩ ታዳጊዎቹን ፊደል የሚያስቆጥር ቄስ ማግኘት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ በሰው በሰው ማፈላለግም ጀመሩ፡፡

‹‹ከጐጃም የመጡ በአካባቢያችን የሚኖሩ አንድ ክርስቲያን ሰው ነበሩ፡፡ ልጃቸውም ቄስ ነበሩ፡፡ የሚኖሩትም ጐጃም ነበር፡፡ አባትየውንም ስለጉዳዩ አነጋገርናቸው፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ቄሱ ወደ ሀና ቦሶቂ መጥተው እንዲያስተምሩን ተደረገ›› ሲሉ ፊደል ለመቁጠር የነበረውን ፈተና ያስታውሳሉ፡፡

‹‹የሚቀረን ነገር የለም፡፡ ሁሉንም እንማራለን፡፡ ቅዳሴና ዳዊት መድገምም የትምህርታችን አካል ነበሩ›› የሚሉት አቶ አብደላ በትምህርታቸው ጠንካራ ከሚባሉት ተርታ እንደነበሩና ትምህርቱን በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፊደል መቁጠር እንደቻሉ ያስታውሳሉ፡፡ ማንበባቸው በርካቶችን አስገርሟል፡፡ ማንበብ መቻላቸውን ያስመሰከሩት የግብር መክፈያ ደረሰኞችን በማንበብ ነበር፡፡ በንባባቸው በወላጆቻቸውና በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ አድናቆትን አተረፉ፡፡ ወላጆቻቸውም ኮሩባቸው፡፡ ‹‹የእኔ ወረቀት ማንበብ ተአምር ሆነ›› ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ መልኩ ጥቂት እንደቆዩ በአጋጣሚ በተፈጠረ አለመግባባት የኔታ ማስተማራቸውን አቋርጠው ወደ ሌላ አካባቢ ሄዱ፡፡ የአቶ አብደላ ትምህርቱም እዚያ ላይ ተቋረጠ፡፡ በወቅቱ ማንበብና መጻፍ ችለው ስለነበር የትምህርቱ መቋረጥ ወላጆቻቸውን አላስጨነቃቸውም፡፡ ይሁንና በትምህርት ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንደሚቻል የሚያምኑት አቶ አብደላ የትምህርቱን መቋረጥ መቀበል አቃታቸው፡፡ በአጋጣሚው ልባቸው ተሰበረ፡፡ በተለይም የቄስ ትምህርቱ ከተቋረጠ በኋላ ወደሌላ አካባቢ ተዘዋውሮ ዘመናዊ ትምህርት መማር የጀመረውን አብሮ አደግ ጓደኛቸውን ሲመለከቱ በጅምር በቀረው ትምህርታቸው የበለጠ ያዝኑ ነበር፡፡

በዚህ መልኩ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ማንኛውንም መሰዋዕትነት ከፍለው የተቋረጠ ትምህርታቸውን ከዳር ለማድረስ ወሰኑ፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ወደሚሰጥበት አካባቢ ጠፍተው በመሔድም ትምህርት ለመጀመር ሙከራ አደረጉ፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ የሚያስመዘግባቸው ተያዥ የግድ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ አቶ አብደላም ሙከራቸው ባለመሳካቱ እያዘኑ ወደ ወላጆቻቸው ተመለሱ፡፡ ሁኔታቸውን የተመለከቱ ወላጅ አባታቸው ግን አቶ አብደላ የተመኙትን ትምህርት ያገኙ ዘንድ በቅሎ ጭነው ወደ ከተማ ገሰገሱ፡፡ ተያዥ ሆነዋቸውም አስመዘገቧቸው፡፡

አስፈላጊውን ነገር ሁሉ አሟልተው ዘመድ ጋር ሆነው እንዲማሩ አደረጉ፡፡ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ ከተማሩ በኋላ ግን ሌላ ፈተና ተጋረጠባቸው፡፡ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም እንደደረሰ የተሰማቸው ቤተሰቦቻቸው ትምህርቱን አቋርጠው ትዳር እንዲይዙ ይጐተጉቷቸው ገቡ፡፡ ‹‹መማር ነበር የምፈልገው፡፡ ላለማግባት ብዙ ጥሬም ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ በመሆኑም ደብተሬን ለተማሪዎች አከፋፍዬ ሚስት አገባሁኝ›› በማለት ለሁለተኛ ጊዜ ትምህርታቸውን አቋርጠው ትዳር የመሠረቱበትን አጋጣሚ ያወሳሉ፡፡

ትዳር ይዘው ልጅም ወለዱ፡፡ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት እንደማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ በግብርና ስለነበር ውሏቸው በማሳቸው ላይ ሆነ፡፡ የትምህርታቸውን ነገርም ዕርግፍ አድርገው ተውት፡፡ ነገር ግን እንደአጋጣሚ ሆኖ በመኖሪያ አካባቢያቸው ትምህርት ቤት ተከፈተ፡፡ ለዓመታት ሲመኙት የነበረን ዕድል በቅርባቸው ያገኙት አቶ አብደላ ከልጃቸው ጋር ተመዝግበው ያቋረጡትን ትምህርት ካቆሙበት ቀጠሉ፡፡

መማራቸው በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ወጣ ያለ አመለካከትና ለነገሮች ያላቸው ግምት የተለየ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በአካባቢው ገዥዎች የሚደርስባቸውን ጫና እንደ ሌሎቹ አሜን ብለው አይቀበሉም፡፡ ለምን ሲሉ ይጋፈጧቸዋል እንጂ፡፡ በወቅቱ ለነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው፡፡ ትምህርት ቤት መግባታቸውና ፊደል መቁጠራቸው ደግሞ ንቁ እንዲሆኑ፣ በአገሪቱ ስለነበሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችም  መረጃዎች እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል፡፡

‹‹በአካባቢው ከነበሩ ባላባቶች ጋር አልስማማም፡፡ ብዙጊዜ እጋጭ ነበር፡፡ ከየአቅጣጫው ይነሣ የነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ ሁሉ እሰማ ነበር፡፡ ደስ ያሰኘኝ ነበር፡፡ ብዙ ሳይቆይም ለውጡ መጣ፡፡ እኔም እንደገና ትምህርቴን አቋርጬ በዚያው ለውጡን ተቀላቀልኩኝ›› በማለት በዘመኑ በአገሪቱ በነበሩ አርሶ አደሮች ዘንድ ተፅዕኖ መፍጠር ያስቻላቸውን እንቅስቃሴ አንድ ብለው የጀመሩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

በ1967 ዓ.ም. በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና ሥራ ዘመቻ አጋጣሚ የቀበሌ ገበሬ ማኅበር ተቋቋመ፡፡ መጻፍና ማንበብ የሚችሉት አቶ አብደላም የቀበሌው ገበሬ ማኅበር ፀሐፊ ሆነው ተመረጡ፡፡ ጥሩ ይንቀሳቀሱ ስለነበር ከ6 ወራት በኋላ የወረዳው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው እንዲሠሩ ተሾሙ፡፡ እዚያም ብዙ አልቆዩም፡፡ ‹‹ትንሽ እንደሠራን በአውራጃ ደረጃ የመደራጀት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሥርዓት የሚጠሉ ተራማጅ የሚባሉና ያለፈውን ሥርዓት ናፋቂ ወግ አጥባቂዎች የሚባሉ አሉ፡፡ እኔ ከተራማጆቹ ጋር ተሻርኬ በመሥራት የአውራጃ ገበሬ ማኅበር ለማደራጀት እንቅስቃሴ ጀመርኩ›› ሲሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃላፊነታቸው ከፍ እያለ መሄዱን ይናገራሉ፡፡

የአውራጃ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ማደራጀት ግን ቀላል አልነበረም፡፡ በሌላው ጐራ የነበሩት ወግ አጥባቂ ወገኖች ማኅበር ለማደራጀት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ ተከታትለው ያጨናግፉ ነበር፡፡ ማኅበሩን ለማቋቋም የሚደረጉ ስብሰባዎች እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት እንዲበተኑ ያደርጉ ነበረ፡፡ አቶ አብደላም እልህ ከመጋባት ይልቅ ሌላ አማራጭ መጠቀምን መረጡ፡፡ የማኅበሩን መደራጀት አጥብቀው የሚፈልጉ በየአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች በያሉበት በሚስጥር እየተገናኙ እንዲወያዩ ሐሳብ አቀረቡ፡፡ በሐሳባቸው በመስማማትም አርሶ አደሮቹ በሚስጥር እየተሰባሰቡ ይወያዩ ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም የአውራጃ ገበሬ ማኅበር ለማቋቋም ተቻለ፡፡ ለድርጅቱ መቋቋም ትልቁን ሚና የተጫወቱት አቶ አብደላ የአውራጃው ገበሬ ማኅበር ፀሐፊ ሆነው ተመረጡ፡፡

በፀሐፊነት ለአንድ ዓመት ያህል ከሠሩ በኋላ የፖለቲካ ትምህርት የመማር ዕድል አጋጠማቸው፡፡ ይህም የትምህርት ደረጃቸውን አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው እምነት ነበራቸው፡፡ ትምህርቱ ወደሚሰጥበት ደብረ ብርሃን ከተማ ሲደርሱ ግን እውነታው ሌላ መሆኑን ተረዱ፡፡ ያገኙት ዕድል የትምህርት ሳይሆን የውትድርና ነበር፡፡ ግን በአጋጣሚው አልተከፉም፡፡ ወደ ሥልጠናው ገቡ፡፡

‹‹ወደ ማሠልጠኛ የገባሁት በ1969 ሚያዝያ ወር ነው፡፡ የዛኔ የሶማሊያ ጦርነት ነበር፡፡ ዕድሜዬም ከፍ ብሏል፡፡ 35 ገብቻለሁ፡፡ አንዴ ከመጣሁ ወደኋላ አልልም ብዬ ለ3 ወራት ያህል ወታደራዊ ሥልጠና ወሰድኩኝ፡፡ ከዚያም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መረቁን፡፡ ወዲያውም ታጠቅ 300,000 ሚሊሺያ ገብቷል፡፡ እነሱን የምታሠለጥኑት እናንተ ናችሁ› በማለት ሥልጠና እንድንሰጥ መመሪያ አስተላለፉልን›› ሲሉ በአጋጣሚ የገቡበት ሥልጠና ሌላ ኃላፊነት እንደጣለባቸው ይናገራሉ፡፡

በታጠቅ ማሠልጠኛ የሚገኙ ወታደሮችን ለተወሰኑ ጊዜያት ሲያሠለጥኑ ከቆዩ በኋላ ወደመጡበት አገር ተመልሰው በእጃቸው ላይ የሚገኙ የመንግሥት ንብረቶችን አስረክበው እንዲመለሱ መመርያ ተሰጣቸው፡፡ እንደተባሉት ለማድረግም ወደ ኢሉ አባቦራ ሔዱ፡፡ እዚያ ከደረሡ በኋላም ተመልሰው ስለሄዱበት ሁኔታ በወቅቱ ለነበሩ የገበሬ ማኅበሩ አባላት አስረዱ፡፡ እነሱም በሐሳቡ እንደተስማሙ ሁሉ በማግሥቱ ሁሉም የወረዳው ገበሬ ማኅበራት በተገኙበት እንደሚሸኟቸው ነግረዋቸው ተለያዩ፡፡

በማግሥቱ ሲገናኙ ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ‹‹አትሔድም፡፡ በአንተ ምትክ 5 ሰዎች እንልካለን፡፡ አንተ የአውራጃው ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር ሆነህ ሥራ አሉኝ›› የሚሉት አቶ አብደላ በቀረበው ሐሳብ ሳይስማሙ ቀርተው በወቅቱ የነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማሳመን ብዙ እንደጣሩ፣ ነገር ግን እንዳልተሳካላቸው እና የአውራጃው ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው ለመሥራት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ብዙም ሳይቆይ በአውራጃ ደረጃ የነበረው የገበሬ ማኅበር በክፍለ አገርና በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲደራጅ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ‹‹አንተ በአገር አቀፍ ደረጃ ነው የምትወዳደረው ብለው እኔን አስቀርተው በክፍለ አገር ደረጃ የሚወዳደሩ የተወሰኑ ሰዎችን መርጠው ሰጡ፡፡ ነገር ግን ፀሐፊ ሆኖ የሚሠራ ሰው በመጥፋቱ በሁለቱም ደረጃ መወዳደር እንደምችል ተረጋግጦ የክፍለ አገሩ ገበሬ ማኅበር ፀሐፊ ሆኜ እንድሠራ ተመረጥኩኝ›› በማለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንድ ኃላፊነት ወደሌላ እንዴት እየተሸጋገሩ እንደመጡ ይናገራሉ፡፡

የክፍለ አገሩ ገበሬ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ ወዲያው የአገር አቀፍ ገበሬ ማኅበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ የገበሬ ማኅበራትን በማቋቋም ስመ ጥር የሆኑት አቶ አብደላም የመላው ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር (መኢገማ) ሊቀመንበር ሆነው ለመመረጥ በቁ፡፡ ‹‹ማንን እመርጣለሁ ከሚለው ሐሳብ ውጪ እመረጣለሁ የሚለው ነገር ጭንቅላቴ ውስጥ አልነበረም›› ሲሉ አጋጣሚው ፈጥሮባቸው ያለፈውን ስሜት ይገልጻሉ፡፡

‹‹ገበሬው በምርት ሥራ ላይ እንዲበረታ፣ ለአብዮቱ ጥበቃ እንዲወጣ ግፊት እናደርጋለን፡፡ በተለይም አርሶ አደሩን በመሠረተ ትምህርት ፊደል እንዲቆጥር ጥረናል፡፡ በዚህም ትልቅ ለውጥ መፍጠር ችለናል፡፡ 10 ከሚሆኑ የውጭ አገሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ዓለም አቀፍ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ችለናል፡፡ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ቢሆን ያ ሁሉ ጦርነት ባይኖር ደግሞ የበለጠ መሥራት እንችል ነበር›› ሲሉ የደርግ ሥርዓት እስኪገረሰስ የመላው ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት ያከናወኗቸውን ተግባራት ይገልጻሉ፡፡

የደርግ ሥርዓት ሲገረሰስ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን መኮብለል ተከትሎ ብዙዎቹ አመራር ላይ የነበሩ ባለሥልጣኖች ከአገር ወጥተዋል፡፡ አቶ አብደላ ግን ‹‹ምን ያጠፋሁት ነገር አለ? ለምንስ እታሰራለሁ›› በማለት ወደ ጐረቤት አገሮች ከመሰደድ ይልቅ ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለስን መረጡ፡፡ እስሩ ግን አልቀረላቸውም፡፡ ለ3 ወራት ያህል ታስረው ነው የተፈቱት፡፡ ከእስር እንደተፈቱ በሌላ የመንግሥት ሥራ አልተሰማሩም፡፡ ጡረታም የላቸውም፡፡ ኑሯቸውን ለመምራት ወደ አደጉበት የግብርና ሙያ ገቡ፡፡ እስካሁንም ኑሯቸውን የሚመሩት በግብርና ነው፡፡ የ78 ዓመቱ አቶ አብደላ በሥራቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወሳሉ፡፡

በየገበሬ ማኅበሩ ሲያገለግሉ የቆዩትም ‹‹ሥልጣን የመያዝ ፍላጐት ኖሮኝ አይደለም፡፡ አገሬን ስለምወድ ለውጥ ለማምጣት ብዬ እንጂ›› ሲሉ የአሁኑ ትውልድም አገሩን እንዲወድና ከድህነት እንዲያላቅቃት የአባትነት ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡