FOR BETTER OROMIA

የቱለማ ኦሮሞና የሸዋ ስያሜ

ኦሮሞ ከኩሽ ህዝቦች ሁሉ አብላጫና በሰፊ መልክዓ ምድራዊ ይዞታ ላይ ተስፋፍቶ የሚኖር ሕዝብ ነው። እንደ ስፋቱና ትልቅነቱ መጠን ደግሞ ኦሮሞ የተለያዩ ጎሣዎች አሉት። እነርሱም ቱለማ :መጫ :ጉጂ :ቦረና :ገብራ :አርሲ :ኢቱ :ሁምበና: ራያ: የጁ: ከረዩ ሊበን-ወዘተ በመባል ይታወቃሉ። ከነዚህ ዉስጥ የቱለማ ጎሣ አንደኛው ነው። የቱለማ ኦሮሞ በኢትዮጽያ እምብርት ሰፊ የሆነ አካባቢና እንዲሁም ከጥንት[ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ4000 B.C] ጀምሮ የኩሽ ህዝቦች እንደ አንድ ቋንቋ(ኩሽ)ተናጋሪ ህዝብ ሲኖሩበት በነበረ ሥፍራ ላይ እንደ ኦሮሞነቱ ብሎም እንደ ኩሽነቱ ተንሰራፍቶና ሰፍሮ የነበረና ዛሬም በመኖር ላይ ያለ የኦሮሞ አብይ ጎሳ ነው። ከአንዳንድ የኦሮሞ ትዉፊቶች መረዳት እንደሚቻለው ይህ የኦሮሞ ጎሣ በመሃል ኦሮሚያ የሰፈረና ከጊዜ በኋላ ግን ከዚሁ ማዕከል በመነሣት በሁሉም አቅጣጫዎች ለተሰራጩ ኦሮሞዎች ዋና ግንድና መሠረት እንደ ነበሩ ይገለጻል። ለምሳሌ የመጫና ቱለማን የትውልድ ቦታን እንደ አንድ አባት ልጆች በመውሰድ በአሁኑ ጊዜ መናገሻ ወይም ከኮሎቦ የሚገኘው የአጌዱ ጋራ ላይ እንደነበረና በኋላ እንደ ተራራቁ የኦሮሞ አዛውንቶች ይገልጻሉ።

የተለያዩ የታሪክ ፀሐፍት በተለያዩ ጊዜያት በመራጃ በማስደገፍ እንዳረጋገጡት ዛሬ የቱለማ ኦሮሞ(የሸዋ ኦሮሞ)ና የሸዋ አምሃራ የሚኖርበት አካባቢ ቀድሞም የኦሮሞ እምብርትና የጥንት የገዳ አስተዳደር የተጀመረበት ከመሆኑም በላይ ኦሮሞ እንደ አንድ ሕዝብ ከሌሎች የኩሽ ወገኖቹ በመገንጠል ራሱን ችሎ የወጣበት አካባቢም እንደሆነ የረጅም ዘመን ታሪካቸውን በመጥቀስ ያወሳሉ። በመኻከለኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ከፊሉ ሕዝብ በክርስቲያኑ መንግሥት ተገፍቶ ከኖረበት የሰሜን ሸዋ ክልል ማዕከሉ ወደ ደቡብ ከመገፋቱ በፊት የቱለማ ኦሮሞ ይዞታ የአባ ሙዳ (ቃሉ) የኦሮሞ ሐይማኖትና ፖለቲካ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል እንደቆየና ዋና ዋና የሙዳ ሥፍራዎችም በዚሁ ሸዋ ዉስጥ እንደነበር ይነገራል። ነገር ግን የግዥ መደብ ታሪክ ጸሐፊዎች በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተካሄደው ተሐድሶና የኦሮሞ ህዝብን እንቅስቃሴ እንደ መጤና እንግዳ በመቁጠር [የኦሮሞ] ፍልሰት ወይም ወረራ ሲሉ ሲዘግቡ ቆይተዋል ነገር ግን የነበረው እንቅስቃሴ የገዥ መደብ ጸሐፊዎች ስደት ይበሉት እንጂ በዘመኑ የነበረው ሕዝቡ ወደነባር ቀኤው የመመለስ ሂደት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

የቱለማ ኦሮሞ ይዞታ የዳበረና ለሰውና እንስሳትም ተስማሚ በመሆኑ የኦሮሞ ጎሣዎችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች በተለያዩ ጊዜያት ቀደምት መኖሪያ ሥፍራቸውን በመተው ወደዚህ ክልል ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታሪክ ያስገነዝባል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚካሄዱት ፍልሰት የተነሣ የቱለማ ኦሮሞ አጎራባች ሕዝቦችና እንዲሁም ከሩቅ ቦታዎች ፈልሰው የመጡት በዚሁ ጎሣ ይዞታዎች ላይ ሲሰፍሩ እንደነበረም እሙን ነው። ስለዚህ ይህ የ”ሸዋ” ስያሜ አመጣጥ ከእነዚህ የተለያዩ ወገኖች የተገኘ ስያሜ እንደሆነ ይነገራል። ሆኖም ግን ሸዋ የሚለው ስም በማንና መቼ እንደ ተሰየመ የተለያዩ መላምቶች(ሃሣቦች) መኖራቸው አልቀረም።

ካሉት ሃሣቦች ውስጥ አንደኛው ከደቡብ አረቢያ ወገን በመሃከለኛው ዘመን (ከ10ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ) ፈልሰው ከመጡ ህዝቦች ጋር የተያያዘ ነው። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያብራሩት ለመጀመሪያ ጊዜ በቱለማ ምድርና መሃበረሰብ ውስጥ የሠፈሩ የውጭ ሰዎች ከመሃከለኛው ምሥራቅ የመጡ አረቦች እንደሆኑ ይነገራል። እነርሱም ለንግድ ሥራና የ እስልምና ሃይማኖትን ለማስፋፋት የመጡ ነጋዴዎች በተለይም አረበ-ገባ እና ወረሼ የተባሉ ወገኖች እንደሆኑ ይነገራል። ከዚህም በመነሳት ወረ ሼ ከሚለው ስም “ሸዬ” የሚለው ስም በጊዜ ብዛት “ሸዋ” ወደሚለው ስያሜ እንደተቀየረና ለዚህም ለማስረጃም ያህል የአያሌ አካባቢ ስሞች ወደ ዓረቦችና አይሁዶች ስምና ቃል እየተቀየረ እንደነበረ ይታወቃሉ። ከነዚህም መኻከል ወደ ሰሜን ሸዋ (ቱለማ) ያሉትን አያሌ የመንደር ስሞች መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ዳንያ ; ኢፋት (ይፋት) ; ኤፌሶን ; ኤፍራታ ; ማመዶች; ወረሼክ ; ማክሱማይት : ደብረሲና :ማፉድ: አንፆኪያና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይበቃል። በይበልጥ ግን ከቱለማ ኦሮሞ አካባቢዎች ሸዋ ወዳ ተባለው ስያሜ (ስም) የተቀየሩት በይፋት አካባቢ የሚገኙ ውስን የ ዓረብ ሰፈሪ መንደሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል። ይህም ከዓረቦች ስያሜና ሰፈራ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይነገራል።

ከጊዜ በኋላ የሸዋ ነገሥታት ነን ብለው ራሳቸውን በመሠየም በተለይም እንደነ ስብስቴ ነጋሢና ተከታታይ ተወላጆቹ በሐይል የወረሱትና የግላቸው ያደረጉት አካባቢዎችን ሁሉ ቀደም ሲል የከረዩ ; ጂሌ ; አርጡማ ; ቆሪ ; ፉርሴ ; ሊበን ኦሮሞዎች ጥንት ሐገርና እርስት መሆኑ ይታወቃል። እነዚህ ወገኖች የኦሮሞን ይዞታ በኋይል በመቆጣጠር ጠንካራ ኋይልና የሀብት ይዞታ ፈጥረው የሕዝቡን እምነትና (ሃይማኖት) ባህል በማስተው በዘዴና በሐይል ከራሳቸው በመቀላቀል በተለይም እንደነ መንዝ (የላሎና ማማ ምድር : ግቼ ; ቂያ: ሞላሌ: ዱሙጋ: ባሶና ወራናን) የመሳሰሉ ሰፊ መሬት ቀደምት የሸዋ መሪዎች እነ ስብስቴ ነጋሤ :ሣህለ ሥላሴና እንደነ ኋይለ መለኮት እንዲሁም ምኒሊክ 2ኛ ያሉ በአውሮፓ መሳርያ በመታገዝ በተከታታይ ኦሮሞን ከአባት ሀገሩ በመንቀል ሀገር ማቅናት በሚል ስም ዘርፈውታል። ከዚህም በመነሳት በተለይም ከአፄ ምኒሊክ 2ኛ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ቱለማ የሚለው ስም “ሸዋ” በሚለው እየተተካ መምጣቱን የተለያዩ ፀሐፍት ይመሰክራሉ። የሸዋ ስም መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣና ከሰሜን ምሥራቅ የቱለማ ሀገር ተነሥቶ እስከ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ እስከ መኻከለኛ የመጫ ኦሮሞ ይዞታን ጨምሮ ይጠራበት እንደነበረ ይታወቀል።

ሌላው ሸዋንና ስያሜውን አስመልክቶ ያለው ሠነድ የአለቃ ወልድ ክፍሌን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ጠቅሶ ደስታ ተ/ወልድ የፃፈው ነው። እርሱም እንደሚከተለው ገልፆት ነበር።

“ሺዋ /ሺሕዋ/ የሴት ስም የግሼ ባላባት : የወሎ ባላባት የሴት ልጅ ምስ ብዙ ልጆች ስለወለደች አባቷ ልጄ ሽኋዋ አሏት። በዚህ ምክኒያት የልጆቿ ሀገር ሸዋ ተብሎ ተጠራ ይባላል። ሸዋ ከግሼ ጀምሮ ወንጭት በመለስ እስከ አዋሽ ነው።”

የሸዋ ግዛት ከጊዜ በኋላ ግሼን መጨመሩ (የስሙ ከዚያ ሀገር ጋር መተሳሰር ሲገልጽ) ይህ ስም ከዚያ ሀገር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል ወደሚለው እንድምታ ያደርሰናል። ሆኖም ግን ይህንን የሚያረጋግጥ አጥጋቢ መረጃ አልተገኘም።

እንግዲህ ከተለያዩ ምንጮች ከቀረቡ ገለጻዎች በመነሳት ለቃሉ ምንጭነት የትኛዉ ትክክለኛ እንደሆነ ማነጻጸር ተገቢ ይሆናል። ከዚህ ውጭም ቱለማ የሚለው ስም ሸዋ ከሚለው ስም ቀደምትነት እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም። ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ወደፊት ጥልቅ ጥናት መደረግ አለበት: ሆኖም ግን ወደ እውነት የተቃረበ ነው ወይም ሚዛን ደፍቷል ሊባል የሚችለው ከዓረብ ሀገር ከመጡ ሰፋሪዎች ጋር ተያይዞ የቀረበው ጭብጥ ነው። ከዚህም በመነሣት ይህ ሸዋ የተባለው ስም ከትንሽ ቦታ ተነሥቶ በመስፋፋት ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ያደገና መነሻው የቱለማ ኦሮሞ ጥንተ ሀገር መሆኑን እንረዳለን። ቢሆንም ቅሉ ስሙ (ሸዋ የሚለው) የኦሮሞ ቃልም ሆነ ፍቺ የሌለውና የሰፋሪ ሐይሎች ስም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

Source: https://www.facebook.com/mamitti.luke/posts/693200200773219

Leave a comment