FOR BETTER OROMIA

ይድረስ ለአቶ ልደቱ አያሌው፦

(Yaye Abebe)

ከማከብራቸው ፓለቲከኞች አንዱ እርሶ ነዎት። የአገራችን እንጭጭ ፓለቲካን ፊት ለፊት ከተጋፈጡትና ብዙ መስዋዕትነት ከከፈሉ ግለሰቦችም አንዱ እርሶ ነዎት። ሰላማዊ ትግል መንገድ ላይ ያለዎትን አቋምና ፅናት አደንቃለሁ።

ሆኖም በአዲስ አድማስ ላይ የሰጡት ምልልስ* ላይ ስለኦሮሞ ሕዝብ ንቅናቄ ያነሷቸው ሃሳቦች ህፀፅዊ (fallacious) ናቸው። ትችቴን ነጥብ በነጥብ እነሆ።

=========
አዲስ አድማስ፦ አመፅና ግጭቶቹ የመብት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የብሄር አክራሪነት የታከለባቸው ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ልደቱ፦ ህብረተሰቡ በታሪኩ አብሮ የኖረ ህብረተሰብ ነው፡፡ በልዩነት የመኖሩን ያህል ብዙ የአንድነት መገለጫ የሆኑ እሴቶች አሉት፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ግን ሲሰበክ የኖረው ልዩነቱ ነው እንጂ አንድነቱ አልነበረም፡፡ በዚህ ህብረተሰቡ “እኛና እነሱ” የሚል አመለካከት እንዲያዳብር ነው የተደረገው። ይሄ ሂደት ወደ ጠባብነትና ዘረኝነት የሚያመራ አደጋ እንደሚፈጥር ግልፅ ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ይሄን ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ሃገራዊ ራዕይ ሳይሆን አካባቢያዊ ሁኔታን ነው፡፡ እኛ ብሎ “እነሱ” የሚባሉትን የሚጠላ ኃይል ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡ በኔ ሀብት ማንም ሊጠቀም አይገባም ብሎ የሚያምን ህብረተሰብ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡
==========

1. “ህብረተሰቡ በታሪኩ አብሮ የኖረ ህብረተሰብ ነው፡፡”

– አብሮ መኖር ትርጉም የለውም። ተከባብሮ መኖር እንጂ። ወሳኙ ምን አይነት አኗኗር ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። በበረት ውስጥ መኖር ወይም በእስር ቤት መኖር በራሱ ዋጋ የለውም። ዋጋ ሚሰጠው የግንኙነቱ አይነትና ጥራት ነው።

2. “በልዩነት የመኖሩን ያህል ብዙ የአንድነት መገለጫ የሆኑ እሴቶች አሉት፡፡”

– እዚህ ላይ “አንድነት” የሚለው ቃል የተሳሳተ ነው። ‘አንድ አይነት’ ማለትዎ ይመስላል። የምንመሳሰልባቸው እሴቶች አሉ። መመሳሰል ግን የእኩልነት ምልክት አይደለም። እኩልነት ሚለካና ሚሰፈር ነው። ዘመናዊት ኢትዮጵያ የእኩልነት ተምሳሌት አልነበረችም።

3. “ባለፉት 25 ዓመታት ግን ሲሰበክ የኖረው ልዩነቱ ነው እንጂ አንድነቱ አልነበረም፡፡”

ባለፉት 25 ዓመታት የማንነት ግንባታ (identity empowerment) ነው የተደረግው። እኔ ዐማራ ነኝ። ዐማራ ነኝ ማለት ፀረ-“አንድነት” መሆን ነውን? ሌሎች ወገኖች “ትግራዋይ ነን” ማለታቸው፤ “ኦሮሞ ነን” ማለታቸው…ፀረ-“አንድነት” ነውን? ሊረዱት ሚገባው አሃዳዊት ኢትዮጵያ በረት እንደነበረች ነው። በግ፥ ፈየል፥ ፈረስ፥ በቅሎ፥ በሬ፥ ላም፥ ዶሮ … አንድ በረት ውስጥ ስለታጎሩ “አንድነት” አላቸው ማለት አይቻልም። ሁሉም እንደ ማንነቱና ምንነቱ የሚኖርበት ሰፊና ምቹ አገር ለመፍጠር ያለፉት 25 ዓመታት ከፍተኛ ሚና ተጫወተዋል። ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ንቅናቄ የሚያመለክተው ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ተገንብቶ ሳለ፥ ሕገመንግስታዊ መብታቸው በግፍና በሰፊው መናዱን ነው። ያ ነው ጉዳዩ።

4. “በዚህ ህብረተሰቡ “እኛና እነሱ” የሚል አመለካከት እንዲያዳብር ነው የተደረገው።”

“እኛና እነሱ” ባለፉት 25 ዓመታት የተፈጠረም ሆነ የዳበረ ነገር አይደለም። ዘመናዊት ኢትዮጵያ በወረራ ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ “እኛና እነሱ” ሲባል ነው የኖረው። ሁለት ማስረጃ ላቅረብ፦ ዳግማዊ ምኒሊክ አርሲን ለመውረር አምስት አመት ወስዶባቸዋል። ያ ለምን ይመስልዎታል? “እኛና እነሱ” ስለነበር ነዋ! ወላይታን ለመውረር ዳ.ሚ. 8 አመት ወስዶባቸዋል። ንጉስ ጦና ያን ሁሉ ጊዜ እምቢ ብሎ የተፋለመው “እኛና እነሱ” ሰለነበረ ነው። “እኛና እነሱ” መኖሩ “አንድነት” ለመፍጠር እንቅፋት አድርገው ለማቅረብ ከሆነ እጅጉን ተሳስተዋል። የአገር አንድነት ሚከበረው “እኛንም” “እነሱንም” በእኩልነት ሚያስተናግድ አገር ሲኖር ብቻ ነው። ሌላ መንገድ የለም። እርሶ የልቅ-ዴሞክራሲ ርዮት (liberal democracy) አቀንቃኝ ሆነው እንዴት የበዝሃነት (plurality, diversity) ፅንስን ዘነጉት?!

5. “ይሄ ሂደት ወደ ጠባብነትና ዘረኝነት የሚያመራ አደጋ እንደሚፈጥር ግልፅ ነው፡፡”

ኦሮሞ “ኦሮሞ ነኝ” ስላለ፥ ታሪኩን፣ ወጉን፣ ባህሉን፣ አመለካከቱን (mythology) ከፍ አድርጎ ስላነገበ እንዴት ወደ “ጠባብነት” ይመራዋል? እንዴትስ ወደ “ዘረኝነት” ይመራዋል? በማንነት መኩራት እንዴት ወደ “ጠባብነትና ዘረኛነት” ያመራል? ማንነትን በግልፅ ማንገብና መላበስ ጤ-ነ-ኝ-ነ-ት እንጂ “ጠባብነት” አይደለም። በዳበሩ ልቅ ዴሞክራሲያዊ አገሮች እንኳንስ የብሔር ማንነትን ማስተናገድ አይደለም … የጋብቻ መብትም ለተመሳሳይ ፆታ ይሰጥ ብለው የርሶ ምዕራባዊያን የርዕዮት ጓዶች በሚታገሉበት ወቅት (እርሶ ያንን ይደግፉሉ ማለቴ አይደለም፥ አላውቅምና)፥ እርሶ የብሔር ማንነት ግንባታ እንደ አደጋ ፈጣሪ ሲያመለክቱ አልገባኝም። ወይ ርዮቱ አልገባዎትም ወይ የጓዳ ትምክህተኛ ነዎት። እኔ እንዲያውም ልቅ ዴሞክራሲ አራማጆች የብሔር ማንነትን ግንባታ ከብሔር ድርጅቶች በላይ ልትንከባከቡት ይገባል ባይ ነኝ።

6. “አሁን እያየን ያለነው ይሄን ነው፡፡”

አሁን እያየን ያለነው ከመቶ አመታት በፊት የኦሮሞን መሬት በጉልበት ሲቀራመት ለኖረውንና ዛሬም ለቀጠለው ንጥቂያ ኦሮሞ ወጣቶች እምቢ ማለታቸውን ነው። እምቢተኝነቱ ከሌሎች እምቅ ብሶቶች ጋር ተደምሮ የማያባራ ታሪካዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ Nov 12 ላይ ፈነዳ! ፍንዳታው በኢትዮጵያ ታሪክ ተከስቶ የማያቅ በ-ኦሮሞ፣ ለ-ኦሮሞ፣ ከ-ኦሮሞ የተከወነ ነው። ኦሮሞ ባንኗል። ይሄንን ታላቅ ሕዝብ ከእንቅልፉ እንደባነነ አንበሳ ጋሜውን አሻሽተን ማረጋጋት እንጂ “ጠባብ ዘረኛ” ማለቱ አደጋ ነው። ኸረ ሲያገሳስ ምን ሊሉ ይሆን?!

7. “አሁን እያየን ያለነው ሃገራዊ ራዕይ ሳይሆን አካባቢያዊ ሁኔታን ነው፡፡”

ኤዲያ! ፓለቲካ እኮ ሁልጊዜ አካባቢያዊ ነው። (Politics is always local) አገራዊ ሲሉ ለመሆኑ ኦሮሞ አድዋ ላይ ለኢትዮጵያ አጥንቱ መከመሩን ረስተዉት ነው? ለራሱ መብትና ጥቅም የሚታገል በሚሊዮን ሚቆጠሩ ቁቤ የቆጠሩ (‘ፊደል የቆጠሩ’ ካልኩ ኦሮሞ ወዳጆቼ አይለቁኝም) ብሩህ ኦሮሞ ወጣቶች የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለይተው በማወቃቸውና ለፓለቲካ ትግል አቅመ ዓዳምና ሄዋን መድረሳቸውን እያየን ያለነው። ይሄ አገራዊ ራዕይ ነው!!! ኦሮሞ ለመብቱ መሞቱ አገራዊ ራዕይ ነው! ቅድመ አያቶቹ አድዋ ላይ ሲሞቱ ብቻ ነው አገራዊ ራዕይ ሚባለውን? ኦሮሞ ለኦሮሚያ ጥቅም ሲሞትም አገራዊ ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያንና ኦሮሚያን ለይቶ ማየት እንዴት ይቻላል? አይቻልም።

8. “እኛ ብሎ “እነሱ” የሚባሉትን የሚጠላ ኃይል ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡”

በመጀመሪያ ፓለቲካ ጥቅም ማስከበሪያ ሂደት ነው። ሌላው ጉዳይ ፓለቲካ አንገት ላይ የታሰረ ቃጭል ነው። ኦሮሞ ሁለቱን እጆቹን አንስቶ፥ ግንባሩ ላይ አድርጎ፥ ደሙን ማፍሰሱና ለጥቅሙ መሞቱ እንዴት በጥላቻ ይታያል? “እነሱ” ያሉትስ ወርቁና ሰሙ ምንድን ነው? የልቅ ዴሞክራዲ አቀንቃኝ ከሆኑ ድብቅ አቀራረብ አይመጥንዎትም። ግልፅ ይሁኑ።

9. “በኔ ሀብት ማንም ሊጠቀም አይገባም ብሎ የሚያምን ህብረተሰብ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡”

ስህተት! የተፈጠረው ‘የአያት ቅድመ አያቶቼ መሬትን ነጥቆ እኔን ኩሊ፣ ሚስቴን ኩሊ፣ ልጆቼን ስደተኛ፣ ሱሰኛ፣ የወሲብ ሰራተኛ ማድረግን አላምንም፣ አልቀበልም” የሚል ትውልድ ነው። ፓለቲካ ጥቅም ማስከበሪያ መንገድ ነው። ጥቅም፣ ጥቅም፣ ጥቅም! ሌላው ቃጭል ነው … ኪል ኪል ኪል። የኦሮሞ ወጣት ይኼ ገብቶታል። እርሶስ?

ከአክብሮት ጋር!

ያዬ አበበ