FOR BETTER OROMIA

የምሥራቅ ኦሮሚያ ተረጂዎች በእጥፍ ጨምሯል

ሰሞኑን በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመቃኘት የጋዜጠኞች ቡድን ምሥራቅ ኦሮሚያ ተንቀሳቅሰው ነበር ፡፡የጋዜጠኞች ቡድን  ከተመለከታቸው አካባቢዎች መካከል፣ ምሥራቅ ኦሮሚያ የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ ከወራት በፊት የነበሩት ተረጂዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃረን አልዪ እንደገለጹት፣ እስካሁን¬ 549,000 ተረጂዎች ተለይተው ዕርዳታ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድርቁ አሁንም ለውጥ ሳያሳይ በመቀጠሉ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ብቻ ከ320 ሺሕ በላይ ተጨማሪ ተረጂዎች የመንግሥትን ዕርዳታ የሚሹ በመሆናቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር 900 ሺሕ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ለእነዚህ ተረጂዎች የሚሆን ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ የተጠየቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞንም በተመሳሳይ በድርቅ የተጎዱ ተረጂዎች ቁጥር እንደጨመረ፣ የዞኑ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ቶፊቅ ገለጻ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ሲሰጣቸው የነበሩት ከ500 ሺሕ በላይ ተረጂዎች ነበሩ፡፡ በጥር ወር ግን የተረጂዎች ቁጥር ከ720 ሺሕ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የሁለቱም ዞኖች የሥራ ኃላፊዎች የተረጂዎቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ በሁለቱም ዞኖች እስካሁን ዕርዳታ ሲሰጣቸው የነበሩት የባሰ ችግር የነበረባቸው ናቸው፡፡ ድርቁ እየተራዘመ በመምጣቱ ግን የተሻሉ ናቸው የተባሉትንም ጭምር ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳም ባለፈው ዓመት 14,404 የነበሩ ተረጂዎች ቁጥራቸው ከ51 ሺሕ በላይ ሆኗል፡፡

እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ፣ በ2007 የምርት ዘመን ይገኛል ተብሎ የታቀደው 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነበር፡፡ በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ግን ሊገኝ የሚችለው ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል ያነሰ ነው፡፡ በምዕራብ ሐረርጌም የሚጠበቀው ምርት ቀድሞ ከተገመተው በእጅጉ ያነሰ እንደሚሆን ታምኗል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የድርቅ ተጎጂዎች ከሆኑ ወረዳዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሳርቱ ሙክታር እንደሚሉት፣ መንግሥት ዕርዳታ እየሰጣቸው ቢሆንም ዕርዳታው በቂ አይደለም፡፡ በአንድ ቤተሰብ 15 ኪሎ ስንዴ እየተሰጣቸው መሆኑንና ሦስት ጊዜ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከስንዴው ጋርም አንድ ሊትር ዘይት ቢሰጣቸውም ይህ ግን በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ የውኃ ችግሩ ግን እጅግ የከፋ መሆኑን የሚገልጹት የሚደጋ ቶላ ወረዳ ነዋሪዎች፣ በአጋጣሚ በዘነበው ዝናብ በአንድ ኩሬ ላይ የተጠራቀመ ውኃ ለከብቶቻቸውም ለራሳቸውም ይጠቀሙበታል፡፡

ቀድሞ ለመጠጥ ይጠቀሙበት የነበረው ኩሬ በመድረቁ መንግሥት በቦቴ የሚያመጣውና የሚያሠራጨው ውኃ የማይዳረስ ስለሆነ፣ አንዳንድ ነጋዴዎች አምጥተው የሚሸጡትን አንድ ሊትር ውኃ በአንድ ብር እየገዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሃሮን አሊዪ እንደሚሉትም በአካባቢው ያለው የውኃ እጥረት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ካለው ሁኔታ አንፃር በዞኑ የከፋ ችግር ላለባቸው ወረዳዎች 30 የውኃ ማመላለሻ ቦቴዎች እንደሚያስፈልጉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹17ቱን አግኝተን በእነዚሁ ቦቴዎች እያከፋፈልን ነው፡፡ የጠየቅናቸው የውኃ ቦቴዎች ከመጡ የውኃ ሥርጭቱ መጠን ይጨምራል፤›› ይላሉ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያገኛቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም በምሥራቅ ሐረርጌ በድርቅ የተጎዱ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የሚደረግላቸው ዕርዳታ በቂ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ያለመሆኑን ነው፡፡ የሚሰጣቸው ዕርዳታ ባለመኖሩም አንዳንዶቹ ወደ ጂቡቲና ወደተለያዩ አካባቢዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

እንደነ አቶ ዓሊ ኢንድሪስ ያሉት ደግሞ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ፕሮጀክት ላይ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው በቀን 30 ብር እየተከፈላቸው ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ከዚህ ሲብስም በደህናው ጊዜ ያደለቧቸውን ከብቶች እየሸጡ ነው፡፡

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎችም ከብቶቻቸው በድርቁ ምክንያት ስለተጎዱና ከችግር ለማምለጥ ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲያወጧቸው ዋጋ እየወደቀባቸው መቸገራቸውን፣ ሲብስም ቀድሞ እስከ 20 ሺሕ ብር ይሸጡ የነበሩትን ከብት ከአምስት ሺሕ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

በዚህ ወረዳ ከ77 ሺሕ በላይ ከብቶች አስቸኳይ የመኖ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ቢገልጹም፣ እስካሁን ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣሂር ፊኒኖ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በቶሎ መኖውን ካላቀረበላቸውም በከብቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

አቶ አብደላ መሐመድ የሚኤሶ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ያለው ድርቅ የከፋ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕርዳታ ካላገኙም ችግር ውስጥ የሚወድቁ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ችግሩ ለከብቶቻቸው ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ እስካሁን በ2007 የምርት ዘመን ፍሬ ያላፈራውን የበቆሎና የማሽላ አገዳ እየመገቡ ያቆዩዋቸው ቢሆንም፣ ከብቶቻቸው አሁን ምንም መኖ የላቸውም፡፡

አቶ አብደላ ያሏቸውን ከብቶች ከሚኖሩበት መንደር ውኃ ወዳለበት አካባቢ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2007 የምርት ዘመን የዘሩት በቆሎና ማሽላ ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ፣ በእጃቸው የቀሩትን ከብቶች በአነስተኛ ትንሽ ኩሬ ውኃ እያጠጡ ከኩሬ ዳር ማደርና መዋል ከጀመሩ ሦስት ቀናት አልፏቸዋል፡፡

ይህችም ኩሬ ብትሆን ከአንድ ሳምንት በላይ የሚቆይ ውኃ የሌላት መሆኑን የገለጹት አቶ አብደላ፣ ሦስት ልጆቻቸውን ጥለው እሳቸው ከብቶቻቸውን ለማዳን ሲወስኑ ከከብቶቻቸው ሦስቱን ሸጠው ለቀለብ የሚሆን ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በመተው ነው፡፡

እንደ አቶ አብደላ ገለጻ እስካሁን አምስት ከብቶቻቸውን አርደዋል፡፡ ከሚሞቱ ብለው የወሰዱት ይህ ዕርምጃ በቀሪዎቹ ከብቶቻቸው ላይ እንዳይደርስም የቻሉትን ያህል ውኃ ወዳለበት መጓዝ ግዴታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ትልቁ ችግር ውኃ ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ሰዎችም ሆኑ ከብቶች ውኃ ለማግኘት በእጅጉ ተቸግረዋል፡፡ ድርቁ ያስከተለው ጉዳት ከዚህም በኋላ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዚህችው አነስተኛ ኩሬ ዳርቻ ሪፖርተር ያገኛቸው ሌላው አርሶ አደር እየደረሰ ያለውን ጉዳት በማየት ዕርዳታ ያልተደረገላቸው መሆኑን በሐዘኔታ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው የሚመጡት የመንግሥት ኃላፊዎች ችግሩን ሰምተው ይሄዳሉ እንጂ ዕርዳታ እያደረጉልን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የልጆቻችን ሰውነት ቀንሷል፡፡ ከትምህርት ቤትም እየቀሩብን ነው፤›› የሚሉት እኚሁ አርሶ አደር፣ ለውኃ ችግር መፍትሔ ካልመጣ አካባቢውን ለቆ መሄድ ግድ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ የፈጣሪ ጉዳይ ስለሆነ ከዘራነው አላገኘንም፡፡ ከፈጣሪ በታች ያለን መንግሥት ነውና ዕርዱን ብለናል፤›› ያሉት አርሶ አደሩ፣ አሁንም ይህ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ይማፀናሉ፡፡

በሚኤሶ ወረዳ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ዕርዳታ እየተሰጣቸው አለመሆኑን ቢገልጹም፣ የሚኤሶ ወረዳና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ኃላፊዎች ዕርዳታ እየተሰጠ ነው ይላሉ፡፡

የሚኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ከማል፣ ‹‹በአጋጣሚ ያነጋገርናቸው በወረዳው ሊረዱ ይገባል ተብለው ከተያዙት ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ፤›› በማለት የአልተረዳንም ጥያቄ ለሚያነሱት አርሶ አደሮች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ የተሻሉ ናቸው የተባሉትም ዕርዳታ የሚሹ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ዕርዳታ ሊሰጣቸው ይገባል ከሚባሉት ውስጥ ይካተታሉ ብለዋል፡፡

ከዕርዳታ ሥርጭት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ ዕርዳታ እየተሰጠ አለመሆኑን ሲገልጹም ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ያላካተተ አሠራር እንዳለ ያመለክታሉ፡፡

የዕርዳታ አሰጣጡ ፍትሐዊ ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉም የሚናገሩ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ግን የዕርዳታ አሰጣጡ በግልጽነት የሚካሄድ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህ ዕርዳታ አሰጣጥ ላይ ችግር ቢፈጠር ወዲያው ዕርምጃ የሚወሰድበት አሠራር ተዘርግቷል ይላሉ፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር እንደገለጸው ለቁጥጥር ከአስተዳደር፣ ከዓቃቤ ሕግና ከሕዝብ አደረጃጀት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኤሶ ወረዳ ዲርባ ቀበሌ ደግሞ ከዕርዳታ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የቀበሌው የሥራ ኃላፊና የጎጥ አመራሮች እንዲታሰሩ መደረጉን፣ የወረዳው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የቀበሌው ሊቀመንበርና የጎጥ አመራሮች የታሰሩት በዕርዳታ ዕደላው ወቅት የአንዳንዱን ቤተሰብ ቁጥር በማሳነሳቸው፣ የአንዳንዶቹን ደግሞ ቁጥራቸውን በመጨመር የተሻለ መጠን ያለው ዕርዳታ እንዲሰጣቸው በማድረጋቸው ነው፡፡

ወረዳው ይህንን መረጃ በሕዝብ ጥቆማ ካገኘ በኋላ ባደረገው ማጣራት፣ ድርጊቱ መፈጸሙ በመረጋጡ ዕርምጃው ለመውሰድ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

በሁለቱም ዞኖች ያለው የከፋ ድርቅ በሰው ሕይወት ላይ ሞት አላስከተለም ተብሏል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ብቻ እስካሁን ከ2,200 በላይ ከብቶች መሞታቸውን የወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

ድርቁ ባስከተለው ችግር የተሰደዱ አሉ የሚባለውን ያስተባበሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ በዚህ አካባቢ ያለ ነዋሪ ወደ ጂቡቲ መሄድና መምጣት የተለመደ በመሆኑ በድርቁ የተሰደዱ ናቸው ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ እንዳይሰደዱ በቂ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንፈልግም ብለው የሚሄዱ አሉ፤›› ብለዋል፡፡ በወረዳቸው ደረጃ የበለጠ ዕርዳታ የሚያስፈልገው ተረጂ ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ ስለሚጨምር ለዚህ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በሁለቱም ዞኖች መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በፈቃዳቸው አዋጥተው ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መጠባበቂያ ፈንድ ውስጥ ተይዟል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት ተከታታይ ዕርዳታዎችን እንደሚያደርግ በእርግጠኝነት አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ  http://ethiopianreporter.com/