FOR BETTER OROMIA

Z9 ጦማሪያን በመጀመሪያ ለምን ታሰሩ?

ከከተማ ዋቅጅራ* | October 2015

Zone9_Bloggers2015

መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ በፈለገው ግዜ የሚያስር በፈለገው ግዜም የሚፈታ ህግ ያለባት አገር ሆናለች። ድንቅ የሚል ጉዳይ ነው። ኸረ እባካችሁ ጠይቁልኝ … ይቺ አገር የማን ናት? ለአሳሪውና ለፈቺው ህግ መብት ሰጥቶ ለታሳሪው እና ለተፈቺው ህግ የሚከለክው።

ኸረ ደግማችሁም ጠይቁልኝ … ወያኔ ያለ-ምክንያት ሲያስር ዝም የሚለው ህግ ያለ-ምክንያት ሲፈታ ዝም የሚለውን የህግ መብት የሰጠው ማን ነው? የጸሃፊስ አሸባሪ የት አገር ነው ያለው? ብዕር ፈንጂ ሆነ እንዴ በወያኔ መንደር? ወይስ በነሱ እውቀት ደረጃ የተማረን ኃይል በተማረ ቋንቋ መመለስ ስለማይችሉ እውቀትና እውነት በነሱ ድርጅት ውስጥ ስሌለ ተብሎ እውቀት ያላቸውንና እውነትን የሚናገሩ ሰዎች በአገራቸው በግፍ መታሰር፣ መንገላታት፣ መሰቃየት፣ መገደል አለባቸው እንዴ? የህዝብ አመጽ እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑት አንባገነን መንግስታቶች ናቸው።

ይህንንም በታሪክ አተናል አሁንም በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ይሄ ነው። ህዝብ የግፍ አገዛዝ እና የጭቆና ኑሮ ሰልችቶት በቃኝ ብሎ ከዳር እስከ ዳር አጋጣሚዎችን እየጠበቀ እና ያቺ ቀን ለአንባገነኖች መቀበሪያ እንደሆነች ያወቀው የአንባገነኖች የግፍ እና የጭቆና አገዛዝ አስመርሮት ነው።

ከዚህ ቀደም እንዳየነው ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ብቻ ወያኔን የሚተቹ እና የሚቃወሙ በመሆናቸው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። አሳሪው በምን ህግ እንዳሰረ ሳይታወቅ ፖለቲከኞችን ወደ እስር ቤት አስገባቸው። በኋላም ከብዙ የእስር እና የስቃይ ግዜ በኋላ ፍርድ ቤቱ ነጻናቸው ቢላቸውም እስካሁን ግን አልተፈቱም – ከጥቂቶች በስተቀር። ለፍርድ ያልቀረቡ በፖለቲካ ሰበብ የታሰረው በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን እንዳሉም ልብ ልንለው ይገባል። አሁን እነዚህ ጦማሪያን ፊርድ ቤቱ ነጻ ናቸው ቢላቸውም ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ሰዎች ላይ እንዳየነው አይነት ፊርድ ቤቱ ቢፈታቸውም ወያኔ ላይፈታቸው ይችል ይሆናል። በአገራችን በነጻነት የመኖሩ መብት የኢትዮጵያኑ ሁላ እንጂ የወያኔ አይደለም ስለነጻነታችን ፈቃጅም ከልካይም ሊሆን አይችልም።

ያለምክንያት ለታሰሩት፣ ያለምክንያት ግዜአቸው ለሚያልፍባቸው፣ ያለምክንያት ለሚሰቃዩት፣ ያለምክንያት ከስራ ገበታቸው ለሚባረሩት እና የስራቸው ግዜ በእስር ላሳለፉት፣ የሞራል እና ሌሎችንም ካሳ ተከፍሎአቸው አሳሪዎቹ ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል።

ብዙኃኑ ጋዜጠኞች፣ ጸሐፊያኖች፣ ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች፣ እሯጮች፣ እንዲሁም ሌሎችም ከሚወዱቷት አገር የሚሰደዱት አገራቸውን ጠልተው ሳይሆን በሚደርስባቸው ህገ-ወጥ ድርጊት በደል ሲያንገፈግፋቸው ነው። መንግስት ተብዬዎች ከሚያደርስባቸው ግፍ በመሸሽ አስቸጋሪውን የስደት ኑሮን ይመርጣሉ።

አሁን ለነዚህ ጦማሪያኖች ለመፈታታቸው ዋስትናቸው ምንድን ነው? ለመታሰራቸውስ ምክንያታቸው ምንድነው? ያለምክንያት ማሰር ያለ ምክንያት መፍታት ሲጀምር አንድ መንግስት ሲጨንቀው እና ፍራቻ በውስጡ ሲገባ ነው። ድንጋጤ ወደ ቤቱን ሲወጥረው ነው። ነገር ግን የህዝብ ጥያቄ ወይንም ትግል መሆን ያለበት ወያኔ ሲያስር ውይ ሲፈታ ደግሞ እሰይ ሳይሆን የኛ ጥያቄ ህግን ለማፈን በመጠቀም በስልጣን ላይ ቁጭ ብሎ የሚባልገውን የወያኔ አገዛዝ እስኪወድቅ ቆርጦ መታገል እና በኢትዮጵያ ውስጥ ህግ የበላይ ሆኖ እስከምናይ ድረስ ኢትዮጵያኑ ያለ-ምንም ፍራቻ ለነጻነቱ መታገል አለበት።

ካለበለዛ በየትኛው የህግ ትእዛዝ እንደታሰሩ ሳያሳውቅ ያሰረ መንግስት በየትኛው የህግ ትእዛዝ እንደፈታ የማያሳውቅ መንግስት ነገስ በድጋሚ እነዚህ ጦማሪያን አልያም ፖለቲከኞች አልያም ጋዜጠኖች እንደማይታሰሩ ምን ዋስትና አለ? ነገስ በነጻነት ሃሳባቸውን በብዕራቸው እውነትን ለህዝባቸው ሲያሳውቁ አሸባሪ የሚል ህግ ተመዞባቸው በድጋሚ አለመታሰራቸው ምን ዋስትና አለ? ለነዚህ ኢትዮጵያዊያን ጦማሪያኖች ዋስትናቸው ወያኔ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። አንባገነኖች ተገርስሰው ህዝብ የመረጣቸው መሪ እና ህዝቡን የሚያገለግል መንግስት እስከሚኖረን ድረስ ትግሉ ይቀጥላል። ነጻነት ለጦማሪያን። ነጻነት ለፖለቲከኞች፣ ነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ!

* ከተማ ዋቅጅራ: waqjirak@yahoo.com