FOR BETTER OROMIA

የእሬቻ ማዕከላትና አከባበር

የኦሮሞ ብሔር በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ ሕዝቦች አንዱና ትልቁ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ህዝብ በረጅም ዘመናት ታሪኩ ዉስጥ የራሱ በሆነ የባህልና የእምነት ሥርዓት ሲመራ የነበረ ነው። ይህም ሥርዓት ገዳ -Gadaa- በመባል ይታወቃል። የገዳ ሥርዓት በዘመኑ ሙሉና ህብረተሰቡን በየትኛውም መልኩ ሊያገለግል የሚችል ሥርዓት ነበር። በገዳ ሥርዓት ውስጥ የእምነት ተቋማት እንዲሁ ከፍተኛ ሥፍራ አላቸው። እነዚህ የህዝቡ የእምነት ተቋማት የሚመሩት በ”ቃሉ”-Qaalluu- (መንፈሳዊ መሪ) ሥርዓት ነው። እሱም በገዳ ሥርዓት አካል የተዋቀረ ነው። ገዳ የኦሮሞ ኢኮኖሚያዊ ፤ ማሃበራዊ ፤ ፖለቲካዊና የእምነት ዘርፎች በውስጡ የተደራጁበት ሥርዓት ነው። በኦሮሞ ባህል ውስጥ ከሚገኙ የእምነት ሥርዓቶች አንዱ እሬቻ-Irreecha- ነው። ከእሬቻም ሌላ አያሌ የገዳና ሓይማኖታዊ በዓላት አሉ። እሬቻ ምስጋና ለዋቃ (ለአምላክ) ለማቅረብ የሚከናወን ሥርዓት ነው። የሚከናወነው የምሥጋና ተግባር እንዲሁ በቦታና በጊዜ የተወሰነ ነው። ይህም በአያንቱዎች- Ayyaantuu-(የቀን ቀመር በሚያዉቁ ሰዎች) የሚወሰን ነው።

ኦሮሞ ይህንን የእሬቻ በዓል በየዓመቱ በሚያከብርበት ወቅት “የፈጠረንን አምላክ እናመልካለን : ተፈጥሮን ይዘን እናመልካለን” በማለት የአምላክን ተፈጥሮአዊ ሥራ ያደንቃሉ : ይለምናሉም: በፍቅር ያወድሱታልም። በኦሮሞ ሐይማኖት ውስጥ አያንቱዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ሕዝቡም እነሱ በጠቆሟቸው የእምነት ቦታና ጊዜ ላይ በመሰብሰብ ምሥጋና እንዲያቀርቡ ይነገራል። የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ሊከናወን የሚችል ቢሆንም ታላላቅ የሚባሉት ግን በሁለት ቦታዎች የሚከናወኑት ናቸው። እነዚህም የተራራ ላይ እሬቻና የመልካ-Malkaa- /ወንዝ ላይ የሚደረግ እሬቻ በመባል የሚታወቁ ናቸው። ከዚህም አንጻር ሲታይ የጩቃላ (ዝቋላ) ተራራና ሆራ አርሰዲ ላይ የሚካሄደው እሬቻ ታላቅና ከሁሉም የሚልቅ እንደሆነ ይነገራል።

የተራራ ላይ እሬቻ

ይህ የምሥጋና በዓል የሚካሄደው በተራራ ላይ ሲሆን ጊዜውም የበጋ ወራት አልፈው የበልግ ዝናብ በሚጠበቅባት ወቅት ነው። ቀደም ሲል የነበሩት ወራት(የበጋ ወራት) በዝናብ እጦት ምክኒያት እንሰሳት በድርቅ ሲጠቁ የቆዩበት ወቅት ስለነበረ ፤ ይህ በመሆኑ በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ መላው ህዝብ ተጠራርቶ እርጥበትና ልምላሜ ወዳለበት ምድር /ተራራ/ በመዉጣት አምላክ የበልግን ዝናም ይሰጣቸው ዘንድ ልመና ያደርሳሉ።

የመልካ በጅረት ላይ የሚደረግ እሬቻ

ይህኛው ሐይማኖታዊ ሥርዓት የሚካሄደው ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ (የጸደይ ወቅት) ወይንም ከመስከረም ወር አጋማሽ በኋላ (ከ22-25 ባሉት ቀናት ውስጥ በአንዱ) የሚከናወን ነው። በዚህ ወቅት በታላላቅ ወንዞችና ሐይቆች አጠገብ የእሬቻው ሥርዓት ይካሄዳል። የመስከረም ወር በ”ቢራ”-Birraa- መግቢያ ላይ ስለ ሆነ ብዙዉን ጊዜ ይህ እሬቻ “የብራ በዓል” በመባል ይታወቃል። ባንዳንድ አከባቢዎች ደግሞ ይህ የእሬቻ በዓል የሚከበርበት “የችሎት መክፈቻ ዕለት” እየተባለም ይጠራል። ይህም ባለፉት የክረምት ወራት በወንዝ ሙላት የተነሳ ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶች ሁሉ የሚገናኙበት ስለሆነ ይህ እንደ ታላቅ የደስታና ፈንጠዝያ ቀን ይወሰዳል።

በመሆኑም ከውንዙ ውዲህና ወዲያ ማዶ ያሉ ኦሮሞዎች ተሰባስበው ” መሬዎ! መሬዎ! –(Mareewoo!… Mareewoo!) … ” በማለት አምላካቸውን እያመሰገኑና እያወደሱ ወዳ መልካው ይሄዳሉ። የእሬቻው ሥርዓት በአባ መልካው (ባለ ይዞታ)ና በአባ ገዳዎች ምርቃትና ቡራኬ ከተከፈተ በኋላ ቀረው ታዳሚ ለምለምና እርጥብ ሣር እንዲሁም የፀዳይ አበባን በመያዝ ከውንዙ ዳር ሆነው ከውኋው እየነከሩ አምላካቸውን እያመሰገኑ በጋራ ያከብሩታል። ምህረትና ቡራኬውንም ይጠይቃሉ። የልመናው ዓላማ ዋቃ (አምላክ) ዝናብን ፤ ሠላምንና ትውልድን እንዲሰጣቸው ፤ ሰላም እንዲያወርድላቸው ወይንም የዘር ፍሬያቸውን እንዲያበዛላቸውና ለወግ ማዕረግ እንዲያበቃቸው ፤ ዋቃ(አምላክ)ን መለመን(መጣየቅ) ነው።

በዚህም መሠረት ኦሮሞዎች ለብዙ ዘመናት ወዳ ሆረ አርሰዲ ወንዝ በመውረድ በጋራ የምስጋና ሥርዓት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። “ሀርሰዲ” የሰው ስም ሲሆን እርሱም በሊበን ጎሳ ውስጥ “አባ መልካ” የነበረ ሰው ነው። ስፍራው እንዴት ሊመረጥ እንደቻለ የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። በዚሁ ሥፍራ ሁሉም ኦሮሞዎች እንደ ቅዱስ የአምልኮ ስፍራና የምስጋና ማቅረቢያ ስፍራ በዓላቸውን ከጥንት ጀምሮ በዚሁ ሲፍራ ሲያከብሩ ቆይተዋል። ዛሬም እንደ ጥንቱ በዓመት አንዴ በዚሁ ሆራ (ሀርሳዲ-ቢሾፍቱ) ላይ የእሬቻ በዓል በብዙ ኦሮሞዎች (በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ) ዘንድ በድምቀት ይከበራል።

—————————–
Baga Irreecha bara 2014tiin isin gahe!!!
Kan Baranaa geenyee kan bara dhufuutiin nu gahi…!!!

 

Leave a comment