FOR BETTER OROMIA

ኢሬቻ: የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት መገለጫ

የኦሮሞ ህዝብ  በኢትዮጲያ ከሚገኙት ክልሎች ዉስጥ በቆዳ ስፋትና በህዝብ ቁጥር ከፍተኛዉን ድርሻ የያዘ እና ከጥንት ጀምሮ ለረጅም ጊዜያት የራሱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በገዳ ሥርዓት ስር ተደራጅቶ ተግባራዊ በማድረግ ሲተዳደር የቆየና ከገጠሙት ጨቋኝ ሥርዓቶች አገግሞ የራሱን የባህል እሴት ለተዉልዱ ማቆየት የቻለ ነዉ፡፡

Irreechaa Hora
ኢሬቻ ደግሞ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑት  ዉስጥ አንዱ ሲሆን ፣ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በተለያዩ ቦታዎች በስፋት የሚከበር የባህል እሴትና  የኦሮሞ ህዝብም በፈጠረዉ አንድ አምላክ ብቻ በ( ዋቃ ወይንም ፈጣሪ) በማመን ክረምቱ በሰላም አልፎ ፤ አደይ አብቦ ፤ ጸደይ ሲገባ ፈጣሪዉን  እያመሰገነ፣ እንደዚሁም  ደግሞ በጋዉ ተራዝሞ ደርቆ ችግር እንዳይከሰት ክረምቱ በሰላም እንዲገባ የሚማጸንበት ሥርዓት መሆኑን የሚገልጽ ነዉ፡፡ ይህ ሥርዓትም በሁለት ዓይነት የአከባበር ሁኔታዎች ኢረቻ መልካና ኢሬቻ ቱሉ በመባል በህዝቡ ዘንድ ይታወቃል፡፡
ኢሬቻ ቱሉ
ኢሬቻ ቱሉ የሚካሄደዉ፣ የበጋ ወቅት  ተጠናቆ ፤ የክረምቱ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ሲሆን፣ ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ ካልጣለ የድርቅ ችግር በመከሰት  ሰዉ እና እንስሳት ስለሚጎዳ፣ ህዝቡ አስቀድሞ ይህ ችግር እንዳይደርስ በየካቲት ወር አጋማሽ አከባቢ  ከፍ ባለ ተራራ ላይ በመዉጣት ጥላ ባለዉ አከባቢ ላይ ቆመዉ ፈጣሪያቸዉን ክረምቱ በሰላም እንዲገባና ፈጣሪም ዝናም እንዲያዘንብ ዪማጻናሉ፤ ይህም ኢሬቻ ቱሉ በመባል ይታወቃል ፡፡
ኢሬቻ መልካ
ኢሬቻ መልካ ደግሞ የሚከናወነዉ ክረምቱ ተጠናቆ ጸደይ ሲገባ በመስከረም ወር አጋማሽ አከባቢ  ሲሆን ይሄዉም በክረምቱ ወቅት የሞላዉ ዝናብ ቀንሶ ከማዶ ማዶ በወንዙ ሙላት ተራርቆ የነበረዉ ዘመድ ወዳጅ ተገናኝቶ ለፈጣሪዉ ምስጋናን በማቅረብ ደስታዉን የሚገልጽበት ወቅት ነዉ፡፡
በዚህ ወቅት ወዳጅ ዘመድ ከወንዙ ማዶ  ተጠራርቶ የባህል ልብስ በመልበስ እርጥብ ሣር እና አደይ አበባ ይዘዉ  ‹‹ ፈጣሪን እንለምናለን ፤ በፈጠረዉም ነገር ፈጣሪን እናደንቃለን ……. ኦ …. ያ…ማሬዎ….. ማሬዎ ›› በማለት ክረምቱ በሰላም ተገባዶ፤ ጸደይ አብቦ፤ ወዳጅ ዘመድ በሰላም በመገናኘቱ፣ ፈጣሪን እያመሰገኑ ወደ ወንዝ ወርደዉ ሙላቱ የቀነሰዉን ወንዝ በእርጥብ ሳሩና በአደዩ እየነከሩ  በክረምት ዝናብ ጎርፍ የደፈረሰዉ ወንዝ ዉሃዉ መጥራቱን የጸደይ መገለጫ መሆኑን እያሳዩ፣ ቀጣዩ ወቅት የሰላም የጤና እንዲሆን ፈጣሪን እየተማጸኑ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘዉ ሆራ ሀርሰዲም ከጥንት ጀምሮ የኦሮሞ ቱለማዎች አንድ ላይ በመሆን በድምቀት  የኢሬፈናን ሥርዓት ሲያከናዉኑበት የነበረ ቦታ በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜም ይህ ቦታ አሴቱን ጠብቆ ለትዉልድ በመተላለፍ በዓመት አንድ ጊዜ የኦሮሞ ህዝብ በሙሉ በእንድነት በሥፍራዉ በመገኘት በሚያደርገዉ ደማቅ ሥርዓት ባህሉን ለዓለም ያስተዋዉቃል፡፡