FOR BETTER OROMIA

የማስተር ፕላኑ ጦስ

በኦሮሚያ የአዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን ከሚገኙ 37 ከተሞች ውስጥ አንዷ በሆነችው ለገጣፎ ከተማ በጊራር ባረክ ቀበሌ አርሶ አደሩ አቶ መለስ ኡርጌ፣ ኅዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በእርሻቸው ላይ ከዘሩት ጤፍ አቅራቢያ ሳር እያሳጨዱ ነበር፡፡

በአካባቢው አልፎ አልፎ ከሚታዩ ጎጆዎች ውጪ ሰፊ የእርሻ መሬት ነው የሚታየው፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሱት ሠልፎች፣ ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ ፖለቲካዊ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ ከተቃውሞው ዋነኛ አጀንዳዎች አንዱ ደግሞ የልዩ ዞኑ ገበሬዎችን ከእርሻ ማሳቸው የሚያፈናቅል ነው የሚለው ወቀሳ ነው፡፡

‹‹እኔ ማስተር ፕላኑ አያሳስበኝም፡፡ በማስተር ፕላኑ የተነሳ መሬቴን አጣለሁ የሚል ፍርኃት የለኝም፣›› በማለት አርሶ አደር መለስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይሁንና በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፋ ባለው ከተሜነት የተነሳ መልካቸው ፈጽሞ እየተቀየረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአርሶ አደሩ አቶ መለስ ስሜት ማረጋገጫ ለመስጠት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ ከአቶ መለስ እርሻ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ አስቀድሞ የእርሻ መሬት የነበሩ፣ አሁን ፋብሪካዎችና የቅንጦት ቪላዎች የተገነቡባቸውን ቦታዎች ማየት ይቻላል፡፡ ከእነዚህም አንዱ በኦሮሞ ባለሀብቶች በዶ/ር መሰለ ኃይሌና በአቶ ዓለማየሁ ከተማ ባለቤትነት ሥር ያለው ካንትሪ ክለብ ዴቨሎፐርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. ለገጣፎ ላይ 70 ሔክታር ተረክቦ ሥራ የጀመረው ኩባንያ የገነባቸውን ቤቶች እንደ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ላሉ ባለፀጎች አስረክቧል፡፡

‹‹ገበሬውም ሆነ ሕዝቡ ልማትን አይቃወምም፡፡ ትልቁ ችግር የካሳው መጠንና ገበሬዎቹን ወደ ሌላ ሥፍራና ሥራ መሠረታዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው የማሸጋገር ሥራ ነው፤›› ያሉት አርሶ አደር መለስ፣ ቢቻል ቢቻል ከቀያቸው በምንም ምክንያት ሆነ በየትኛውም መጠን ባይፈናቀሉ እንደሚመርጡ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹በሔክታር የሚከፈለው የካሳ ክፍያ መጠን ላይ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ በአቅራቢያችን አንድ የቱርክ ኢንቨስትመንት ለአንድ ካሬ ሜትር ስድስት ብር የካሳ ክፍያ ከፍሏል፡፡ ለአንድ ሔክታር መሬት 60,000 ብር ይሰጣል ማለት ነው፡፡ እኔ ገበሬ ነኝ፡፡ በዚህ ብር ምን እሠራበታለሁ? ስለዚህ እርሻዬን እያረስኩ ቤተሰቤን ብደግፍ እመርጣለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኅዳር 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በአምቦ፣ በጊንጪና በምዕራብ ወለጋ የተጀመረው ተቃውሞ ሦስተኛ ሳምንቱን የጨረሰ ሲሆን፣ የተቃውሞ ሠልፉ በክልሉ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ተስፋፍቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና አልፎ አልፎም በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ዋና ተሳታፊነት ሲካሄድ የቆየው ተቃውሞ የኋላ ኋላ ነዋሪዎችንም አካቷል፡፡

በተቃውሞ ሠልፉ የተሳተፉ አካላት ዋነኛ ጥያቄ መንግሥት ማስተር ፕላኑን እርግፍ አድርጎ እንዲተው ማድረግ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገውን ማስተር ፕላን ለመቃወም በሚያዝያና በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. የተጠሩት ሠልፎች የዘጠኝ ሰው ሕይወት መቅጠፋቸው፣ ለብዙዎች መጎዳትና መታሰር ምክንያት መሆናቸው፣ ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የደረሰው ጉዳት መንግሥት በይፋ ከተቀበለው እጅግ የላቀ ነው የሚል ቅሬታም ይቀርባል፡፡

በተመሳሳይ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በነበረው ተቃውሞ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ዜጎች ነፃነታቸውን እያጡ ነው፣ ንብረት እየወደመ ነው፣ የትምህርት ጊዜ እየተስተጓጎለ ነው፡፡ መንግሥት እስካለፈው ዓርብ ድረስ የጠፋው የሰው ሕይወት አራት እንደሆነ ገልጿል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ለሪፖርተር እንደገለጸው ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ሪፖርት ደርሶታል፡፡

ተቃውሞውን ለማረጋጋት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀማቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች ኅዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት መንግሥት የፀጥታ ኃይሎቹን ዕርምጃ እንዲገመግም፣ በነፃና በገለልተኛ ወገን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡ ሌሎች ዘገባዎችም በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በመተኮስ ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ኃላፊዎችና የክልሉ ባለሥልጣናት ግን ይህን ወቀሳ አስተባብለዋል፡፡ የኦሮሚያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በተቃውሞውና በብጥብጡ ከተማሪዎች በተጨማሪ የታጠቁ ኃይሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ለብሉምበርግ እንደተናገሩት ደግሞ፣ በብጥብጡ ምክንያት 20 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታየ የሚገኝ አንድ የፖሊስ ጣቢያን ለመቆጣጠርም ሙከራ ተደርጎ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የማይታወቀው ማስተር ፕላን በድንገት ሌላ ተቃውሞ ያስነሳበት ምክንያት ለአንዳንዶች እንቆቅልሽ ቢሆንም፣ በቅርቡ የኦሮሚያ ከተሞች ማሻሻያ አዋጅ በጨፌ (በክልሉ ምክር ቤት) መፅደቁ የተቃውሞው መነሻ መሆኑን የኦፌኮ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹አዋጁ የኦሮሚያ ከተሞች ስምን መቀየር፣ አንዳቸውን ከአንዳቸው መቀላቀል፣ ለልማት ሲባል ነዋሪዎችን ማፈናቀልና የመሳሰሉ ጉዳዮች ማካተቱ አሳስቦናል፡፡ ተቃውሞ ከቀረበበት ማስተር ፕላን ጋርም ግንኙነት አለው፡፡ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ካለው ደካማ የመልካም አስተዳደር ሪከርድ፣ ለፌዴራሊዝምና ለዴሞክራሲ ካለው ታማኝነት አንፃር ነዋሪው የነበረውን ተስፋ መቁረጥና ብስጭት በዚህ ተቃውሞ አብሮ የገለጸ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ተሰማና የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ንጉሤ መንግሥቱ ግን አዋጁ ከማስተር ፕላኑ ጋር ግንኙነት እንደሌለው ተከራክረዋል፡፡ አቶ ንጉሤ፣ ‹‹በከተሞች ላይ የተሻለ አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲኖር ለማድረግ ክልሉ የተሻሻለውን የከተሞች አዋጅ ጨፌው በቅርቡ አፅድቋል፡፡ ከተሞች ሙሉ በሙሉ የሚያገኙትን ገቢ ለራሳቸው መሠረተ ልማቶች ማስፋፊያ እንዲያውሉ የሚያደርግ አዋጅ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ በከተሞች የነበረውን የከተማና የቀበሌ አስተዳደር በመባል የሚታወቁትን የአስተዳደር እርከኖች ለአስተዳደር እንዲያመችና የሕዝቡን ጥያቄ በአፋጣኝ መመለስ እንዲያስችል፣ ከሁለቱ መሀል የወረዳ አስተዳደር እንደ ሦስተኛ አስተዳደር እርከን ተደርጎ እንዲዋቀርም የደነገገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማስተር ፕላኑ በጨረፍታ

ይህ ላለፉት ሁለት ዓመታት ውዝግብ ሲፈጥር የነበረና ለመጠነ ሰፊ ጉዳት ያበቃ ማስተር ፕላን ምን ቢይዝ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ከይዘቱም በላይ ሰነዱ የተዘጋጀው በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በአዲስ አበባ አስተዳደር በጋራ መሆኑ፣ የተቃውሞ ሠልፉ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ልትስፋፋ ነው ከሚለው ቅሬታ ጋር ቀጥተኛ ተቃርኖ ያለው ይመስላል፡፡

ከማስተር ፕላኑ ሰነድ ማየት እንደሚቻለውና መንግሥትም በተለያዩ መድረኮች እንደገለጸው፣ ዋናው የማስተር ፕላኑ ዓላማ የአዲስ አበባና የልዩ ዞኑን ነዋሪዎች ሕይወት ለማሻሻልና ለአገሪቱ ልማትና ዕድገት መሠረት ለመሆን ሁለቱ የአስተዳደር አካላት በትብብር እንዲሠሩ ማስቻል ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ ለ25 ዓመታት ያህል እንዲያገለግል የታቀደ ሲሆን፣ በአካባቢው የበለፀጉ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችን ለመፍጠርና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስብ አካባቢ ማድረግም ሌላኛው ዓላማ ነው፡፡ አዲስ አበባ ያላትን የተሻለ አቅምና አገልግሎት የመስጠት ዕድል በልዩ ዞኑ ወዳሉ ከተሞች በማስፋፋት የጋራ ዕድገትን ማፋጠንም የማስተር ፕላኑ ግብ ነው፡፡ እንደ መንገድ፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ባቡር፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና፣ ፋብሪካ፣ ቱሪዝም፣ ቤት፣ የባህል ማዕከልና የገበያ ማዕከል ያሉ መሠረተ ልማቶችን በጥራት በመገንባት በመጪዎቹ 20 ዓመታት በእጥፍ ያድጋል ተብሎ የሚገመተውን ነዋሪ ሕይወት ለማሻሻልና ለማዘመንም ያቅዳል፡፡

መንግሥት ዕቅዱ የጋራ ፍላጎትን መሠረት ያደረገና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ዕቅድ አወጣጥ ሥርዓት ለመገንባት ያለመ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ታዲያ የመንግሥት ዕቅድ ዜጋውን ተጠቃሚ ማድረግ ከሆነ ዕቅዱ ይህን ያህል ውዝግብ ያስከተለው ለምንድነው የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ መልሱ ደግሞ ተቃውሞው ከማስተር ፕላኑ ይዘት ይልቅ፣ ዕቅዱን ለማውጣት ያነሳሳው ምክንያትና ውጤቱ ላይ ያነጣጠረ ይመስላል፡፡

የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት

ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገሮች ተርታ የተሠለፈች መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ አገሪቱ ለዚህ የኢኮኖሚ ስኬት እያበቃኝ ነው የምትለው የልማታዊ መንግሥት ሞዴል፣ በተፈጥሮው ውሳኔ አሰጣጥን ከላይ ወደታች የሚጭን ነው ተብሎ ይተቻል፡፡ እርግጥ ይህ ሞዴል ዴሞክራሲያዊ ነው በማለት አሳታፊና ከታች ወደ ላይ የሚሄድ የውሳኔ አሰጣጥን እከተላለሁ በማለት መንግሥት ይከራከራል፡፡ በተግባር የሚታየው አካሄድ ማዕከላዊ ውሳኔ አሰጣጥን አጉልቶ እንደሚያንፀባርቅ ይተቻል፡፡ ይኼው የውዝግብ ምንጭ የሆነው ማስተር ፕላኑም ለዚህ እንደ አብነት የሚነሳ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተመሠረተበት ምዕላድ የፌዴራል የመንግሥት አስተዳደር የተዋረድ ውሳኔ ሰጪነትን የሚያበረታታና ተቋማዊ ቅርፅ የሚሰጥ ነው፡፡ ክልሎችና ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ የደነገገ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ አስተዳደር በነፃነት ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ይጠቅመኛል ባለው የኢኮኖሚ ዕቅድ ላይ እንዲወስን ይፈቅዳል፡፡

በማስተር ፕላኑ ላይ ተቃውሟቸውን የሚያቀርቡ ወገኖች ዕቅዱ በይዘት ደረጃ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ያለመ ቢሆንም፣ በተግባር የጥቂቶችን ሕይወት ለመለወጥና ገበሬውን በማፈናቀል በመሬት ላይ ያለውን ተጠቃሚነት የሚያነሳ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ለሚፈናቀሉት ገበሬዎች የሚሰጠው የካሳ ክፍያም እጅግ አነስተኛ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ወደ ዘበኝነት፣ የቀን ሠራተኝነትና ከከፋም ወደ ልመና የሚያሸጋግር ነው ሲሉ ያመለክታሉ፡፡

‹‹በልዩ ዞኑ የመሬት ዘረፋ እጅግ ተጧጡፎ የሚከናወን ነው፡፡ ለአንድ ካሬ ሜትር አምስት ብር ከፍለው ገበሬውን ካነሱት በኋላ፣ አየር በአየር በሚሊዮን አትርፈው የሚሸጡት የመንግሥት ኃላፊዎች ናቸው፡፡ መንግሥት ራሱ የችግሩ ምንጭ ሆኖ የሕዝብ ብሶትን እያስፋፋ ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ በእነሱ ተሳትፎ የተረቀቀው ማስተር ፕላን የሕዝብ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለን አናስብም፡፡ አዲስ የመሬት ዘረፋ የሚከፍት ዕቅድ ነው፤›› በማለት ዶ/ር መረራ ማስተር ፕላኑን የሚቃወሙበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡

በማደግ ላይ ባለ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ኢኮኖሚ የከተሜነት መስፋፋትን መገደብ ይቻላል ወይ ተብሎ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር መረራ፣ ከተሜነት የሕዝብን ተጎጂነት የማያመጣና የተሻለ ተጠቃሚነትን በማምጣት አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ዜጎችን ከማፈናቀል ይልቅ የልማቱ አካልና ተጠቃሚ ማድረጊያ መንገዶችን ከካሳ ክፍያ ውጪ ማሰብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የፋብሪካ ወይም የሌላ ግንባታ የባለቤትነት ድርሻ ሊሰጣቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ማንም ኢትዮጵያዊ የፈለገበት ቦታ የመኖርና የመሥራት መብት እንዳለው የኦሮሞ ሕዝብ በሚገባ የሚገነዘብና ከሌሎች ብሔር ብሔሮች ጋር አብሮ ለመኖር ችግር የሌለበት ቢሆንም፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የራሱን ጥቅምና መብት አሳልፎ መስጠት አይጠበቅበትም ሲሉ አክለዋል፡፡

መንግሥት ማስተር ፕላኑ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር በመሠረተ ልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት በማስተሳሰር፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ ለመንከባከብና በጋራ ለመጠበቅ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር፣ ወንጀለኞችን በጋራ ለመከላከል ያለመ በመሆኑ፣ ነዋሪዎቹ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ጥራት የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ በተቃራኒ ይከራከራል፡፡

ፖለቲካዊ ጥቅሞች

ማስተር ፕላኑ ገበሬዎችን በማፈናቀል የኢኮኖሚ ጉዳት ከማምጣት ባሻገር ራስን በራስ የማስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎችን የሚሸረሽር እንደሆነም፣ የተቃውሞ ሠልፎቹ ተሳታፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህም በአዲስ አበባ መስፋፋትና የባህል መበረዝ እንደሚገለጽ ይጠቅሳሉ፡፡

ኦሮሚያ የኢትዮጵያን ፌዴሬሽን ከመሠረቱ ዘጠኝ ክልሎች አንዷ ስትሆን፣ በሕገ መንግሥቱ የራሷ የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት ሥልጣን አላት፡፡ የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተወሰነ በመሆኑ፣ የፌደራል መንግሥት የኦሮሚያ ክልል በተሰጠው ሥልጣን ላይ ጣልቃ ሊገባ አይገባም፡፡

ከዚህ ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት በተጨማሪ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዳላት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ይደነግጋል፡፡ ይህ ልዩ ጥቅም የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀሙንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንደሚሆኑም ይጠቅሳል፡፡ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ፣ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተም ይኼው ልዩ ጥቅም እንደሚከበር ሕገ መንግሥቱ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) በታሪክ የኦሮሞ ግዛት ስለነበረች ልዩ ጥቅም በባለቤትነተ የሚገለጽ ነው በማለት የሚቀርብ ክርክር አለ፡፡

የሕገ መንግሥት ጉባዔ ሰብሳቢ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ‹‹በዝርዝር በአንቀጹ ላይ ውይይት አላደረግንበትም፡፡ በችኮላ ነው የታለፈው፡፡ አሁን ሳስበው ይኼ እንደ ድክመት የሚጠቀስ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ዝርዝር ጉዳዮች በሕግ ይወሰናሉ ቢባልም ከ20 ዓመታት በኋላም ይህን ጉዳይ የሚዘረዝር ሕግ አለመውጣቱ ትልቅ ችግር መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት በሚል የሚቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ በተመለከተ ሲናገሩም፣ ከታሪክ አኳያ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ስለመሆኗ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባን የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ አድርጎ ያስቀመጠ በመሆኑ የባለቤትነት ጥያቄው አከራካሪ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ይኼ ምናልባትም በሕዝብ ውሳኔ የሚወሰን ጉዳይ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ የባለቤትነት ጥያቄ እየተነሳ ባለበት ሁኔታ በማስተር ፕላኑ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባ በመስፋፋት የኦሮማያ ልዩ ዞን ከተሞችን ልትጠቀልል ነው በማለት የሚቀርበው ጥያቄ ተቃርኖ ያለው ነው የሚል አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ዶ/ር መረራ ዝርዝር ሕግ ባለመውጣቱ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም እንደማይታወቅ አስታውሰው፣ ‹‹ማስተር ፕላኑ በተቃራኒው አዲሰ አበባ በኦሮሚያ ልዩ ጥቅም እንዲኖራት የሚያስችል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ማስተር ፕላኑ በኦሮሚያ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ላይ ጫና ያሳድራል በሚለው ግምገማ እንደሚስማሙ የገለጹት ዶ/ር ነጋሶ፣ በዕቅዱ መብቱ ይነካል ከሚለው ሥጋት ባሻገር ማስተር ፕላኑ ያስገኛል የተባለውን ጥቅም ኦሮሚያ በራሱ የማይወጣበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹ሲጀመር ሕዝቡን በደንብ ሳያማክሩ ነው ያረቀቁት፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም በተገቢው ሁኔታ ውይይት አላደረገበትም፤›› ሲሉ ዕቅዱ ኦሮሚያ ላይ የተጫነ እንደሚመስላቸው ገልጸዋል፡፡

የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፉ ተሳታፊዎች ማስተር ፕላኑ የአዲስ አበባን ድንበር በማስፋት የልዩ ዞኑን ከተሞች ወደ አዲስ አበባ መቀላቀሉ ብቻ ሳይሆን፣ በንግድና በኢንቨስትመንት የሚመጡ ሌሎች ሕዝቦች በቦታው በስፋት መስፈራቸው የማንነት መሸርሸርና መጥፋትን ሊያስከትል እንደሚችልም ሥጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ በተለይ በልዩ ዞኑ ላይ ኦሮሚያ ያለው ተፅዕኖ እየተዳከመ ኦሮሚኛ ቋንቋ የማይናገሩና የኦሮሞ ባህልን የማያውቁ ነዋሪዎች መበራከታቸው አሳሳቢ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት አንድን አስተዳዳር ለመጠቅለልም ሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ላይ ገደብ ለማድረግ በቅድሚያ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ሰለሚጠይቅ፣ ይህ ሥጋት ከእውነታው የራቀ ነው ሲል ይከራከራል፡፡ አዲስ አበባም ልታድግ የምትችለው ወደ ላይ እንጂ ወደ ጎን ባለመሆኑ መስፋፋት እንደ ሥጋት የሚነሳ ምክንያት እንዳልሆነም አመልክቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግንኙነት በግልጽ የተቀመጠ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግሥቱ በጓሮ በር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደማያስቀርም አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዶ/ር አሰበ ረጋሳ ያሉ ተመራማሪዎች በማስተር ፕላኑ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞ ዋነኛ መነሻ የእምነት ማጣት ነው ይላሉ፡፡ ይህም የሚመነጨው ከሕዝብ ተሳትፎ መገደብና በኦሮሚያ ማንነት ላይ ይደርሳል ተብሎ ከሚሰጋው ጉዳት እንደሆነ ዶ/ር አሰበ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹Why do the Oromo Resist the Master Plan?›› በሚል ርዕስ በጻፉት ትንታኔ ዕቅዱ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዜጎች ላይ የተጫነ ነው ብለዋል፡፡

የመንግሥት ምላሽ

ለሦስት ሳምንት በቆየው ተቃውሞ ከፌደራል መንግሥት፣ ከኦሮሚያ ክልልም ሆነ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ አስተያየት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሰዎች ሕይወት ከጠፋ በኋላ የመጀመሪያው አስተያየት የተሰጠው ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ከአቶ ኢብራሒም ሃጂ ነው፡፡ እንደ አቶ ኢብራሒም ገለጻ የግጭቱ መነሻ ‹‹ፀረ-ሰላም›› ኃይሎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለአራት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑት ሌላ አጀንዳ ያላቸው ‹‹ፀረ ሰላም›› እና ‹‹ፀረ ልማት›› ኃይሎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከሦስት ሳምንት በኋላ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር ታኅሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በተመሳሳይ ተቃውሞው እንዲባባስ ያደረጉት ‹‹ፀረ ሰላም›› ኃይሎች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ይሁንና ግጭቱ እንዲከሰት ለማድረግ ማስተር ፕላኑን ግልጽ ለማድረግ የነበረው ውስንነት በከፊል ተጠያቂ  እንደሆነ አምነዋል፡፡ ‹‹የተቀናጀ የጋራ ዕቅዱ በተገቢው መንገድ ግልጽ አለመደረጉም በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬና ጥያቄ እንዲፈጠር አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡ በዕቅዱ ዙሪያ ግልጽነት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ከሕዝብ ጋር እስኪፈጠር ድረስም በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው ዕቅድ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደማይሸጋገር አረጋግጠዋል፡፡

በማስተር ፕላኑ ፕሮጀክት ቢሮ ያሉ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ግን፣ የዕቅዱን አፈጻጸም ለመከታተል የተቋቋመው የማኔጅመንት ቦርድ ስብሰባ ካደረገ ዓመት ሆኖታል፡፡ በየሦስት ወሩ እየተሰበሰበ ሥራዎችን የመገምገም ኃላፊነት ግን አለበት፡፡ የሪፖርተር ምንጭ ‹‹ሥራው በአዲስ አበባ በኩል ተጠናቋል፡፡ የኦሮሚያ ኃላፊዎች በዕቅዱ ላይ ያሳዩት ፍላጎት አናሳ በመሆኑ ግራ ተጋብተናል፤›› ብለዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በተነሳው ተመሳሳይ ግጭት የኦሕዴድ አባላት እጅ እንዳለበት መንግሥት አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የግንዛቤ ክፍተት ያላቸው እንዲሁም ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ የማይቀበሉ እንዳሉ መገለጹን ሪፖርተር ዘግቦ ነበር፡፡

ይህ ጥርጣሬ በከፍተኛ አመራሮች ጭምር እየተስተዋለ ጉዳዩን ከመብት ጥያቄ አንፃር ከማየት ይልቅ፣ የጥቂት ‹‹ፀረ ሰላም›› እና ‹‹ፀረ ልማት›› ኃይሎች ሴራ እያሉ ማለፍ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመሻት የማያስችል እንደሆነ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

(ለዚህ ዘገባ ሚኪያስ ሰብስቤ፤ ዮሐንስ አንበርብርና ውድነህ ዘነበ አስተዋጽኦ አድርገዋል)

http://vps17307.inmotionhosting.com/~ethiop9/index.php/politics/item/11555-%E1%8B%A8%E1%88%9B%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%88%AD-%E1%8D%95%E1%88%8B%E1%8A%91-%E1%8C%A6%E1%88%B5